ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም ጤና ድርጅት ክትባቶች ኦሚክሮንን መቋቋም አለባቸው አሉ
የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በአሁን ላይ በጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙት ክትባቶች በአዲሱ ኦሚክሮን የቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ከባድ የጤና እክል እንዳይገጥማቸው መከላከል እንደሚችሉ የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊ ተናገሩ።
ኃላፊው ይህን ያሉት በደቡብ አፍሪካ በተደረጉ ሙከራዎች ይህ ቫይረስ በተለይ የፋይዘር ክትባትን ማሸነፍ እንደሚችል ምልክቶች አሉ መባላቸውን ተከትሎ ነው።
ተመራማሪዎች እንደሚሉት ሰዎች በአዲሱ ቫይረስ ሲያዙ የኮሮናቫይረስ ክትባቶች በሰውነታችን የሚፈጥሩ የመከላከል አቅም በእጅጉ ይቀንሳል።
ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶክተር ማይክ ራያን ኦሚክሮን ክትባቶችን ሙሉ በሙሉ የመገዳደር አቅም እንዳለው የሚያሳይ ምንም አይነት ምልክት አልተገኘም ብለዋል።
"እስካሁን ድረስ ሁሉንም አይነት ቫይረሶች መከላከል የሚችሉ ውጤታማ ክትባቶችን አግኝተናል። በኦሚክሮን ምክንያት ከባድ የጤና እክል የሚገጥመው አልያም ሆስፒታል እስከ መግባት የሚደርስ ሰው ይኖራል ብሎ መገመት በጣም ከባድ ነው'' ብለዋል የዓለም ጤን ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊው ዶክተር ማይክ ራይን።
ኃላፊው አክለውም ኦሚክሮን ከዚህ በፊት ከታዩት ሌሎች የኮሮረናቫይረስ ዝርያዎች አንጻር እንደውም ሰዎችም የማሳመም አቅሙ ዝቅተኛ ነው ብለዋል።
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተሰርቶ እስካሁን በሌሎች ተመራማሪዎች ባልተገመገመ አዲስ ጥናት መሰረት ግን የፋይዘር/ባዮንቴክ ክትባት ከኦሚክሮን ጋር ሲገናኝ ውጤታማነቱ 40 በመቶ እንደሚቀንስ አመልክቷል።
ነገር ግን ኦሚክሮን ሙሉ በሙሉ ከክትባቱ እንደማያመልጥ ደርሰንበታል ይላሉ በአፍሪካ ሄልዝ ሪሰርች ኢንቲትዩት ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አሌክስ ሲጋል።
ተመራማሪው እንደሚሉት ከዚህ በፊት የተያዙ ሰዎች እንዲሁም ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች ኦሚክሮንን የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ ነው ካሉ በኋላ ሶስተኛ ዙር ክትባት መውሰድ ደግሞ ይበልጥ የመከላከል አቅምን ከፍ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።
አዲሱ ኦሚክሮን እስካሁን ከ30 በላይ አገራት ውስጥ የተገኘ ሲሆን ሰዎች በክትባትም ሆነ ኮሮናቫይረስ ሲይዛቸው የሚያዳብሩትን በሽታ የመከላከል አቅም ሊቋቋም የሚችል ነው።
ነገር ግን ከዚህ በፊት ከነበሩት የኮሮናቫይረስ አይነቶች አንጻር እስካሁን ቀላል የሚባሉ ምልክቶችን ብቻ ነው ያሳየው። በዚህም ምክንያት ስለ ቫይረሱ፣ ስለ ስርጭቱ እና ስለሚያደርሰው ጉዳት በርካታ መላ ምቶች እየተሰነዘሩ ነው።
መነሻውን በደቡብ አፍሪካ አገራት ያደረገው አዲሱ የኮሮናቫይረስ አይነት ለዓለማችን ተጨማሪ ስጋትን ፈጥሮ ቆይቷል። ይህ አዲስ ዝርያ እስካሁን ከታዩት የኮሮናቫይረስ አይነቶች እጅግ የተለየው ነው ተብሏል።
በበርካታ ብዙ የዘረመል ለውጥ ውስጥ በማለፉ በአንድ ሳይንቲስት "አሰቃቂ" ተብሎ ሲገለጽ ሌላው ደግሞ እስካሁን ከታዩት የከፋ ዝርያ ነው ብለዋል።
የደቡብ አፍሪካው ሴንተር ፎር ኤፒዴሚክ ሪስፖንስ ኤንድ ኢኖቬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ቱሊዮ ዴ ኦሊቬራ ስለዚህ አዲስ ዝርያ ሲናገሩ፤ "ያልተለመደ የዘረ መል ለውጥ ያለው" ሲሆን ከተሰራጩት ሌሎች ዝርያዎችም "በጣም የተለየ ነው" ብለዋል።
በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ደግሞ የፋይዘር ክትባት ኦሚክሮን ላይ የሚኖረው ጥንካሬና ድክምትን በተመለከተ መረጃዎች ይፋ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
እስካሁን ድረስ እንደ ሞደርና፣ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ያሉ እንዲሁም ሌሎች ክትባቶች ከአዲሱ ኦሚክሮን አንጻር ያላቸው ውጤታመነትን በተመለከተ ምንም ጠቃሚ መረጃ አልተገኘም።