ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች 'ቅጣት ይጠብቃል' ሲሉ ባይደን ፑቲንን አስጠነቀቁ
ዩናይትድ ስቴትስ ሩሲያ ዩክሬንን ትወራለች በሚል ስጋት "ከባድ የአፀፋ ምላሽ" ለመስጠት እየተዘጋጀው ነው አለች።
ይህ የአሜሪካ ማስጠንቀቂያ የተሰማው ባይደን ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው።
በተንቀሳቃሽ ምስል እገዛ በተደረገው ስብሰባ ባይደን ሩሲያ ወታደሮቿን እየገነባች መሆኑን ጠቅሰው "ጠንካራ የኢኮኖሚና ሌሎች ቅጣቶች" ሊጣሉ ይችላሉ ሲሉ ለፑቲን ነግረዋቸዋል ተብሏል።
ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬንን የማጥቃት እቅድ የለኝም ትላለች።
ፕሬዝደንት ፑቲን ዩክሬን ጠብ ቀስቃሽ ድርጊት እየፈፀመች ነው በማለት መውቀሳቸውና ወደ ሩሲያ ድንበር ተጠግቶ የቆመው የኔቶ ጦር ምንም እንደማያደርግ ቃል እንዲገባላቸው መጠየቃቸው ተሰምቷል።
በምስጢራዊ የቪድዮ መልዕክት መለዋወጫ ያወሩት ሁለቱ መሪዎች መጀመሪያ ሲገናኙ ሞቅ ባለ ሰላምታ ነበር የጀመሩት። ነገር ግን ለሁለት ሰዓት የተደረገው ኮስተር ያለ ስብሰባ በዝግ ነው የተካሄደው።
ፕሬዝደንት ፑቲን ስብሰባውን ያካሄዱት ሶቺ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሆነው እንደሆነም ተሰምቷል።
ማክሰኞ ዕለት ከተካሄደው የቪድዮ ስብሰባ በኋላ የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ዋሸንግተን በሚቀጥሉት ሳምንታት እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀች ነበር ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
"በ2014 ያላደረግናቸው ነገሮች አሉ። አሁን ግን ዝግጁ ነው" ሲሉ አማካሪው ባለፈው ጊዜ ሩሲያ ዩክሬንን ወራ ክረሚያን ገንጥላ ስትወስድ የነበረውን ጊዜ አስታውሰዋል።
"ብዙ ነገሮችን ተነስተዋል። ፕሬዝደንቱ የአሜሪካ አቋም ምን እንደሆነ በግልፅ አስቀምጠዋል" ብለዋል ሲሉቫን።
ከእርምጃዎቹ መካከል ምጣኔ ሃብታዊ ዕቀባ መጣልና የኔቶ ኃይሎች ለዩክሬን ድጋፍ እንዲያደርጉ ወደ ድንበር የሚሉት ማምጣት ይገኙበታል።
ባይደን የስልክ ልውውጡን ባደረጉ ጊዜ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ታጅበው ታይተዋል።
ምንም እንኳ ሩሲያ ላይ ሊጣለው የታሰበው ምጣኔ ሃብታዊ ዕቀባ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ይፋ ማድረግ ባይፈልጉትም አንድ አዲስ ወደ ጀርመን የሚጓዝ የጋዝ ማስተላለፊያ ቱቦ ለአሜሪካና አጋሮቿ እንደ ማስፈራሪያ እንደጠቀማቸው ተዘግቧል።
"ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ቱቦ ነዳጅ ሲፈስ ማየት ከፈለጉ ዩክሬንን ወረው አደጋ ውስጥ ባይገቡ መልካም ነው" ብለዋል አማካሪው።
ከዚህ በፊት የወጡ ዘገባዎች ዩክሬን በሩሲያ ከተወረረች ጀመርን የጋዝ ማስተላለፊያ ቱቦውን እንደምትዘጋ ለአሜሪካ ቃል ገብታለች ሲሉ አስነብበው ነበር።
በሌላ በኩል ክሬምሊን ባወጣ መግለጫ ፑቲን፤ ኔቶ ወደ ዩክሬን መሬት ዘልቆ ገብቶ ጦሩን በማደራጀት ለፈጠረው ጫና ሩሲያ ልትጠየቅ አይገባም ማለታቸውን ገልጧል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ የባይደን አስተዳደር ለሚሰጣቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ባይደንና ፑቲን ለመጨረሻ ጊዜ በአካል የተገናኙት ባለፈው ሰኔ ስዊትዘርላንድ ውስጥ ነበር። አምባሳደሮቻቸውን ልከው ስለኒውክሌር መሣሪያ ከማውራት ውጭ ግን የረባ ነገር አላነሱም።
ሰኞ ምሽት በነበረው የቪድዮ ስብሰባ ላይ ግን አሜሪካና እንደ ዩኬ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና ጣልያን ያሉ አጋሮቿ ሩሲያን ለመቅጣት ቃል ገብተዋል።
90 ሺህ ገደማ የሩሲያ ወታደሮች የዩክሬን ድንበር አቅራቢያ በተጠንቀቅ ቆመው እንደሚገኙ ታውቋል።
የዩክሬን ባለሥልጣናት ሞስኮው በሚቀጥለው ወር መጨረሻ ጥቃት ለማድረስ ዝግጅቷን ጨርሳለች ይላሉ።