ፌስቡክ ሐሰተኛ ተመራማሪ ጠቅሰው የውሸት መረጃ ያሰራጩ ገጾችን ሰረዘ

ፌስቡክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፌስቡክ መነሻቸውን ቻይና ያደረጉ እና ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት የተወነጀሉ ከ500 በላይ ገጾችን ሰረዘ።

ገጾቹ ዊልሰን ኤድዋርድስ የተባለ ሐሰተኛ የስዊዘርላንድ የሥነ ሕይወት ተመራማሪ ፈጥረው ነበር መረጃ ሲያሰራጩ የቆዩት።

ይህ በእውን የሌለ ግለሰብ፤ "አሜሪካ የኮሮናቫይረስ መነሻ ምርመራ ውስጥ ጣልቃ ገብታለች" እንዳለ በማስመሰል በገጾቹ ሲጻፍ ነበር።

የዚህ ግለሰብ አስተያየቶች በቻይና መንግሥት መገናኛ ብዙኃንም በስፋት ሲሰራጩ ቆይተዋል።

የስዊዘርላንድ ኤምባሲ የተባለው የሥነ ሕይወት ባለሙያ የእውን እንደሌለ ገልጿል።

መጠሪያውን ወደ ሜታ የቀየረው ፌስቡክ እንዳለው፤ በእነዚህ ገጾች ይሰራጭ የነበረው መረጃ "እምብዛም ስኬታማ አልሆነም"።

መረጃዎቹ በአሜሪካ እና ዩኬ እንግሊዘኛ ተናጋሪዎችን፤ በታይዋን፣ ሆንግ ኮንግ እና ቲቤት ደግሞ ቻይና ተናጋሪዎች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው።

ሐምሌ ላይ ዊልሰን ኤድዋርድስ የተባለ የስዊዘርላንድ የሥነ ሕይወት ባለሙያ ፌስቡክ እና ትዊተር ላይ ጻፈ።

የኮሮናቫይረስ መነሻን የሚያጠኑ የዓለም ጤና ድርጅት ሳይንቲስቶች በአሜሪካ ጫና እየተደረገባቸው እንደሆነ ጽሑፎቹ ይጠቁማሉ።

ሲጂቲኤን፣ ሻንጋይ ዴይሊ፣ ግሎባል ታይምስን ጨምሮ ሌሎችም የቻይና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ይህንን ሰው አጣቅሰው ዘገባ ሠርተዋል።

ነገር ግን ነሐሴ ላይ የስዊዘርላንድ ኤምባሲ የተባለው ግለሰብ የፈጠራ ካልሆነ በስተቀር የእውን ሊኖር እንደማይችል ይፋ አደረገ።

ገጹ ጽሑፍ ማውጣት ከመጀመሩ ከሁለት ሳምንት በፊት ከመከፈቱ ባሻገር ፌስቡክ ላይ ያሉት ጓደኞች ሦስት ብቻ ናቸው።

የስዊዘርላንድ ኤምባሲ "ዊልሰን ኤድዋርድስ ተብሎ የተመዘገበ የስዊዝ ዜጋ የለም። በስሙ የታተሙ ጥናቶችም የሉም" ብሏል።

ኤምባሲው የቻይና መገናኛ ብዙኃን የሌለ ግለሰብን ማጣቀስ እንዲያቆሙ አሳስቧል።

ፌስቡክ ጥቅምት ላይ ባወጣው ሪፖርት ጉዳዩን ማጣራቱን አስታውቋል።

ገጾቹ መነሻቸው ከቻይና እንደሆነ እና ከቻይና መንግሥት ጋር ትስስር ያላቸው ሰዎች ከጀርባው እንዳሉም ደርሶበታል።

ሲቿን ሳይለንስ ኢንፎርሜሽን የተባለ የቻይና ድርጅት ውስጥ ከሚሠሩ ሰዎች ጋር የተያያዙ ገጾች እንደሆኑም አክሏል።

ድርጅቱ ለቻይና የሕዝብ ደኅንነት ተቋም የቴክኒክ ድጋፍ የሚሰጥ የመረጃ ደኅንነት ተቋም ነው።

ፌስቡክ 524 አካውንቶች፣ አራት ቡድኖች እና 20 ገጾች እንዲሁም 86 የኢንስታግራም ገጾች ማጥፋቱን ተናግሯል።

የስዊዘርላንድ የሥነ ሕይወት ባለሙያ ነው በተባለ ግለሰብ ስም የወጣው መረጃ መጀመሪያ የተጋራው በሐሰተኛ የፌስቡክ ገጾች ነበር። ከዚያም መረጃው እውነተኛ የፌስቡክ ገጾች ጋር ደርሷል።

የዚህ ግለሰብ ገጽ በማሽን የተፈጠረ ፎቶ አለው። የገጹ መነሻ እውነተኛ እንዲመስልም ቪፒኤን ተሰጥቶታል።

የኮሮናቫይረስ መነሻ በቻይና እና አሜሪካ መካከል ውጥረት ፈጥሯል።