በአሁኑ ዘመን ስለኤችአይቪ ከሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች በጥቂቱ

ፖል ቶርን ቤተሰቦቹን ለመጨረሻ ጊዜ ያያቸው ከአስርት ዓመታት በፊት ነው።

የተለያዩት ልብ በሚሰብር ሁኔታ ነበር፤ የበላበትን ሰሃን ኤችአይቪ ይተላለፍብናል በሚል ፍራቻ ወረወሩት። ግንኙነታቸውም በዚያው አከተመ።

ፖል ኤችአይቪ በደሙ መኖሩ የታወቀው በአውሮፓውያኑ 1988 ነበር። ይህንንም ተከትሎ የነርሲንግ ስልጠና ትምህርቱን ማቆም ነበረበት።

"የ20ዎቹን ዕድሜዬን ያሳለፍኩት በፍርሃት ነው" ይላል።

በአሁኑ ወቅት መኖሪያውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው ፖል ስለ ቫይረሱ ብዙም አያሳስበውም። በቀን አንድ ክኒን መውሰድ እና በዓመት ሁለት ጊዜ ዶክተሩን ከማየት ውጪ ይህን ያህል ህይወቱን የሚያሰጋው ጉዳይ አይደለም።

ህክምና የሚከታተሉና ጤንነታቸውን የሚጠብቁ በደማቸው ውስጥ የኤች አይ ቪ ቫይረስ የሚገኝባቸው ሰዎች እንደ ሌላው ሁሉ ህይወታቸውን በደስታ መኖር እንደሚችሉ ብዙዎች በዓመታት ተረድተዋል።

እንዲሁም ምግብ በመጋራትና አብሮ ጊዜ በማሳለፍ በሽታው ይተላላፋል የሚሉ ያረጁና የተሳሳቱ አመለካከቶች በአብዛኛው ቢጠፋም አሁንም ቢሆን ጎጂ እና የተሳሳቱ መረጃዎች መሰራጨታቸው አልቀረም።

'መድኃኒት አለው'

ኬንያዊቷ ዶሪን ሞራ ሞራቻ በደሟ ውስጥ በኤችአይቪ ቫይረስ ኖሮ የተወለደች ቢሆንም ሁኔታዋን ያወቀችው በ13 ዓመቷ በአውሮፓውያኑ 2005 በተደረገላት ምርመራ ነው።

በአንድ ወቅት በታንዛኒያ ወደ የሚገኝ የባህል መድኃኒት አዋቂ ነኝ የሚል ግለሰብ ዘንድ የሄደችው ዶሪን እሷንም ሆነ እናቷን ከኤችአይቪ እንደሚፈውሳቸው ነገራቸው።

"እሱ የሚሸጠውን ከዕፅዋት የሚቀመሙ መድኃኒቶችን ጠጥተን ከኤችአይቪ ነፃ መሆናችንን አምነን ተመልሰናል" ትላለች።

በመቀጠልም ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ እንዳይባዛ የሚከለክለውን ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት (አንታይሪትሮቫይራል) መድኃኒት መውሰድ አቆመች። ነገር ግን ትንሽ ቆይታ በሽታን የመከላከል አቅሟ በመዳከሟ የሳንባ ምች ታመመች።

በደሟ ውስጥ ያለው የኤችአይቪ ቫይረስ መጠን መጨመሩንና በዚህም የተነሳ ሌላ ኢንፌክሽን ካጋጠማት እንደምትሞትም ዶክተሯ ነገራት።

የኤችአይቪ ቫይረስ ካልታከመ ሰውነት ቀላል ህመሞችን መቋቋም ወደማይችልበት የኤድስ በሽታ ሊያመራ ይችላል።

የባህል መድኃኒት አዋቂ የተባለው ሰውዬም "አጭበርባሪ" እንደሆነ ግልፅ ሆነላት።

ለኤችአይቪ ምንም አይነት ክትባት ወይም መድኃኒት የለውም ነገር ግን ፈውስ አለው ብሎ ማመን የተለመደ ነው ሲሉ የዓለም አቀፍ ኤድስ ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አዲባ ካማሩልዛማን ተናግረዋል።

በቅርቡ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎችም ሁኔታ ተስፋን ፈንጥቋል።

በቅርቡ በአርጀንቲና የምትኖር አንዲት ሴት በራሷ በሽታ የመከላከል አቅም ከኤችአይቪ ነፃ የሆነች ሁለተኛዋ ሰው ሆናለች። ግን እንዴት እና ለምን እንደሆነ እስካሁን ምክንያቱ አልተገለጸም።

'ኤችአይቪ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች ሁልጊዜ በሽታውን ያስተላልፋሉ የሚል እምነት'

ጋናዊቷ ጆይስ ሜንሳህ ከደረሰባት መገለል ነፃ ለመውጣት ነበር ወደ ጀርመን ያቀናችው። ስለ ሁኔታዋ እንደምትናገረው በተሳሳቱ አመለካከቶች የተነሳ ከቅርብ ሰዎች ጋር ካላት ግንኙነት ባሻገር ሥራዋን እንዳጣች ትናገራለች።

በተለይም መገለሉ የሚመጣው ኤችአይቪ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች ሁልጊዜም ቢሆን ለትዳር አጋራቸው ወይም ለልጃቸው የማስተላለፍ ስጋት ደቅነዋል ከሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው ትላለች።

"ግለሰቦች የኤችአይቪ ሁኔታቻውን ለቤተሰቦቻቸው ሲያሳውቁ ... ሰዎች መቶ በመቶ ደኅንነታቸው የተጠበቀ አይደለም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ አላቸው። ኤችአይቪ በደማቸው አለ ማለት ሁሌም በሽታውን ያስተላልፋሉ የሚል እምነት አለ" በማለት ጆይስ ትናገራለች።

እንዲያውም በተጻራሪው ፀረ-ኤችአይቪ መድኃኒቶችን ለረጅም ጊዜ ከወሰዱ በኋላ፣ ሰዎች ቫይረሱን በወሲብም ሆነ በሌላ መንገድ የማያስተላልፉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ።

ኤችአይቪ በደማቸው ያለባቸው ግለሰቦች የዕድሜ ልክ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም ቫይረሱን ከሰው ወደ ሰው ማስተላለፍ ያቆማሉ።

ህክምናዋን በየጊዜው የምትከታተለው ጆይስ አራት ልጆች ያሏት ሲሆን አንዱም ቫይረሱ በደሙ ውስጥ የለም።

ህክምናው በስፋት እየተስፋፋ በመምጣቱም ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ሁኔታው በግማሽ ቀንሷል።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ኑሯዋን በጋና ያደረገችው የጆይስ ሴት ልጅ ቫይረሱ በደሟ ውስጥ አለባት፣ እንዲሁም ሌሎችንም ልታሲዝ ትችላለች በሚል በቅርቡ ትምህርት ቤቷ ወደ ቤቷ እንድትመለስ አድርጓታል።

ኤችአይቪ በደማቸው ያለ ሰዎች የዩናይትድ ኪንግደም የበጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢያን ግሪን "ኤችአይቪ ያለብን ሰዎቸቭ ብዙውን ጊዜ እራሳችንን እንደ በሽታ አምጪ አድርገን እንመለከታለን" ይላሉ።

"ለብዙ ዓመታት ቫይረሱን ለሌላ ሰው አስተላልፋለሁ የሚል ከፍተኛ ስጋት ነበረብኝ።"

ህክምናው ከደረሰበት ደረጃ አንፃር "ቫይረሱን በአሁኑ ወቅት እኔ በጭራሽ ወደሌላ ሰው ማስተላለፍ እንደማልችል ማወቄ ነፃነት ሰጥቶኛል" ይላሉ።

'ኤችአይቪ የለም'

ኤችአይቪ ከዚህ ቀደም እንደሚታሰበው የሞት ፍርድ ባይሆንም፣ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች መደበኛና ጤናማ ህይወት መኖር ቢችሉም፣ አንዳንድ ዘመቻ አድራጊዎች ግን ቫይረሱ የሚናገሩት እንደሌለ መሆኑ ችግርን እየፈጠረ ነው።

"በኤችአይቪ ህክምናና መከላከያው ላይ በዘመናት ውስጥ አስደናቂ ልኅቀቶች ታይተዋል። ነገር ግን ይህ ኤድስ አብቅቷል የሚለው ሁኔታ በመከላከል ሥራው ላይ ችግር እየፈጠረ ነው። በተለይም የኤችአይቪ ፈውስ ፍለጋም ላይ እንዲሁ ጥረቶችን ከማድረግ አንፃር እክል ሆኗል" በማለት ዶክተር ካማልዛማን ይናገራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአውሮፓውያኑ 2020 መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለም ዙሪያ ወደ 38 ሚሊዮን የሚጠጉ ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ያለ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 700 ሺዎቹ ከኤድስ ጋር በተያያዙ በሽታዎች ሞተዋል። ይህም ቫይረሱ በጊዜ ባለመታከሙ ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ ።

ፖል እንደሚለው ታዳጊና ወጣቶች ሰዎች በሽታውን እንደ አዛውንት በሽታ ይመለከቱታል እናም በርካቶች "በአጠቃላይ ዝቅተኛ ግንዛቤ አላቸው" ብሏል ።

"ኤችአይቪ ያለፈ ነገር ነው ብለው ያስባሉ" ሲል አክሏል።

'እኔ ኤችአይቪ የሚይዘኝ ሰው አይደለሁም'

ልክ ወጣቶች እንደ አዛውንት ህመም እንደሚያዩት ብዙዎች ቫይረሱ ወንድ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎችን ብቻ የሚያጠቃ ነገር አድርገው ይመለከቱታል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ካለባቸው ሰዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

ክሪስቲን ስቴግሊንግ የተባሉት የፍሮንትላይን ኤድስ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሠራተኛ ታዳጊና ወጣት ሴቶችን ከሚገድሉ በሽታዎች ዋነኛው ኤድስ እንደሆነ ይናገራሉ።

ነገር ግን ካናገሯቸው ሴቶች ውስጥ በጣም ጥቂቶች ናቸው አደጋውን የተረዱት።

"ሴቶች የወሲብ ግንኙነትን በተመለከተ ጥንቃቄ ማድረግና አለማድረግን በተመለከተ አስቸጋሪ ውይይቶች ማድረግ አለባቸው" ሲሉ ክሪስቲን ስቴግሊንግ ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት በርካታ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም እየተሰራጩ ያሉ የተሳሳቱ መረጃዎች ኤችአይቪ በደማቸው ያለባቸው ሰዎችን ግንኙነቶቻቸው እንዲቋረጥ፣ ሥራ እንዳይኖራቸው እንዲሁም አልፎ ተርፎም ትክክለኛ ህክምናና ምርመራ እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል።