ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ጦርነት የተቀረውን ዓለም ለምን ያስጨንቀዋል?
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ ኬንያ እየተጓዙ ነው። በዋናነት የኢትዮጵያን ጦርነት አስመልክቶ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አሜሪካና ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ለዜጎቻቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። በአስቸኳይ ኢትዮጵያን ለቃችሁ ውጡ እስከማለት ደርሰዋል። የዩኬ አንድ ሚኒስትር እንዲያውም "…በረራዎች ዝግጁ ይሆኑላችኋል" ብለው ነበር።
የነሐሴውን የካቡል ሁኔታ በሚያስታውስ መልኩ ይህ ሁሉ ጥድፊና ሽርጉድ የመጣው፣ የትግራይ አማጺ ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ ማማተር መጀመራቸው መሰማቱን ተከትሎ ነው።
አሁን ድፍን አንድ ዓመት የሞላው ይህ ጦርነት ብዙ ሰብአዊ ቀውስ ያደረሰ ነው። ከዚህ በኋላ ጉዳዩ የኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ ብቻ መሆኑ ያበቃ ይመስላል።
ኃያላን የውጭ መንግሥታት ሳይቀሩ ሁኔታዎች እጅግ እያሳሰባቸው መጥቶ፣ ድምጻቸውንም ከፍ አድርገው መናገር ጀምረዋል። የዲፕሎማሲ ሩጫውም በዚያኑ ፍጥነት ተጠናክሯል።
የአፍሪካና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ውጥረት እየጨመረ የመጣው ይህ ጦርነት አንዴ ከቁጥጥር ውጪ ከሆነ ለቀጠናው ብሎም ለዓለም ዘርፈ ብዙ አደጋ ይዞ እንደሚመጣ ከመረዳታቸው ነው።
አንዳንድ አሐዞች በራሳቸው የችግሩን ስፋት ጮክ ብለው የሚናገሩ ናቸው።
ለምሳሌ አራት መቶ ሺህ ዜጎች በሰሜን ኢትዮጵያ በከፋ የረሀብ-መሰል ሁኔታ ውስጥ ናቸው። እጅግ አስፈላጊ የሚባሉ መድኃኒቶች 80 ከመቶ በጭራሽ የሉም። ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
ከዚህም ባሻገር ደግሞ በርካታ የንጹሐን ግድያዎች፣ ማሰቃየቶችና ወሲባዊ ጥቃቶች በሁለቱም ወገን ስለመፈጸማቸው መረጃዎች በስፋት ወጥተዋል።
ከዚህ ኢሰብአዊ ውጥንቅጥ ባሻገር የዓለም አገራት ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶች የዚች አገር ዕጣ ፈንታ እንደ ራሱ ዕጣ ፈንታ እንዲያስጨንቀው አስገድዷል።
110 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛዋ ናት። ይቺ አገር ለምዕራባዊያን ፍጹም መረጋጋት ርቆታል፣ አደገኛ ቀጠናም ነው፣ በሚሉት የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ሁነኛና የተረጋጋች አገር ሆና ነው የቀጠለችው።
አሁን በጦርነቱ ሳቢያ የለየለት የእርስ በእርስ ፍጅት ቢከሰት ይቺ ትልቅ አገር የባለ ብዙ ብሔሮች አገር ከመሆኗ አንጻር፣ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ከፍተኛ እልቂት ሊመጣ ይችላል የሚለው ስጋታቸው በርትቷል።
እንደሚፈራው አገሪቷ ከፈራረሰች ደግሞ ሚሊዮኖች ኢትዮጵያን ጥለው መሸሻቸው አይቀሬ ነው። ጎረቤት አገራት ይህን ሁሉ ሚሊዮን ስደተኛ የማስተናገድ አቅሙ አይኖራቸውም። ለከፋ የሰብአዊ ምስቅልቅልም ይዳርጋቸዋል።
የባሕር በር የሌላት ኢትዮጵያ ስድስት አገሮችን ትጎራበታለች። ከስድስቱ ጎረቤት አገሮች ሁለቱ በራሳቸው ቀውስ ውሰጥ ናቸው፤ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን።
ሌላኛዋ ጎረቤት አገር ሱዳን ወታደራዊ ፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባት አገር ናት።
ከዚህ ሌላ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ ወታደሮቿ የጥምረት ተልዕኮ ላይ ናቸው። እነዚህ ወታደሮች ከሶማሊያ አክራሪ ኃይሎች ጋር የሚዋጉ በመሆናቸው ለምዕራባዊያን አስፈላጊ ናቸው።
ሁኔታዎች በአገር ቤት ቢባባሱ ይህ ሠራዊት ለሌላ ግዳጅ ወደ አገር ቤት ሊጠራ ይችላል። ይህ ደግሞ በሶማሊያ አክራሪ እስላማውያን እንዲያንሰራሩ ዕድል ሊፈጥር ይችላል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ወደ አፍሪካ ከማቅናታቸው በፊት የኢትዮጵያ መበታተን ለቀጠናው ከባድ ፈተና ይዞ እንደሚመጣ አስጠንቅቀው ነበር።
የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸው ሲነገር ቆይቷል። ይህ የተራዘመ ጦርነት ሌሎች ጎረቤት አገሮችንም የሚጋብዝ ሊሆን ይችላል የሚል ፍርሃት አላቸው።
አንዳንድ የሩቅ አገራት በዚህ ግጭት ከወዲሁ እጃቸውን አስገብተዋል የሚል መረጃም እየወጣ ነው።
ባለፈው ወር ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ቱርክ ለኢትዮጵያ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮን) ለመሸጥ ተስማማታለች። ይህ ስምምነት የቱርክና የግብፅን ግንኙነት ሊያሻክር የሚችልበት ዕድል አለ።
ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ አለመግባባት ውስጥ መሆኗ ነው ይህን የሚያስከትለው።
ኢትዮጵያ ከቱርክ ሌላ ከቻይናና ከኢራን የጦር መሣሪያዎችን እንደገዛች ይነገራል። ኦሪይክስ የመከላከያ ጉዳዮች ድረ ገጽ አንዳንድ ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የሚነሱ በረራዎች እነዚህን መሣሪያዎች የተሸከሙ ናቸው ሲል ዘግቦ ነበር።
ነገሩን ከአሜሪካ አንጻር ብንመለከተው፣ ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ እምነት የምትጥልባት አጋሯ ሆና ቆይታለች። በተለይም ሽብርን በመዋጋት ረገድ አስተማማኝ አጋሬ የምትላት አገር ነበረች።
በሶማሊያ የእስላማዊ አክራሪ ቡድኖችን ኢትዮጵያ የተፋለመች ሲሆን በኢራቅ ጦርነት ደግሞ የአየር ክልሏን ለአሜሪካ የፈቀደች አገር ነበረች። በአፍሪካ ይህን ለማድረግ ከፈቀዱ ጥቂት አገሮች ተርታም ነበረች።
የተረጋጋና መንግሥት በኢትዮጵያ መኖሩ ለአሜሪካ ትልቅ ፋይዳ አለው። ለዚህም ይመስላል አሜሪካ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ በእርዳታ መልክ ለኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ ስታደርግ የነበረው። ይህ አሐዝ ከ2016 እስከ 2020 ብቻ ያለውን የሚያሳይ ነው።
ነገር ግን በቀጠናው የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን የኢትዮጵያ መንግሥትን ከመውቀስ ወደ ኋላ አላሉም።
የመንግሥት የተሳሳተ ፖሊሲ በርካቶች በረሀብ አለንጋ እንዲገረፉ አድርጓል ከማለታቸው በላይ አስተዳደሩን ከሶሪያው ባሻር አልአሰድ ጋር እስከማነጻጸር ደርሰዋል።
አዲስ አበባ በእርግጥም ስጋት ላይ ናት?
የትግራይ ኃይሎች ተከታታይ ወታደራዊ ድልን እያስመዘገቡ በዋናው አውራ ጎዳና ከሰሜን ወደ መሀል አገር ለመዝለቅ ጉዞ መጀመራቸው በአዲስ አበባ ፍርሃት እንዲነግሥ ምክንያት ሆኗል።
ይህን ተከትሎ የአሜሪካ መንግሥት ዜጎቹ አገሪቱን በአስቸኳይ እንዲለቁ ሲያሳስብ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ደግሞ ለ6 ወራት በመላ አገሪቱ የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ደንግጓል። ከዚህም በላይ ዜጎች እንዲዘምቱ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
የአዲስ አበባ አስተዳደር በበኩሉ ነዋሪዎች የጦር መሣሪያቸውን እንዲያስመዘገቡ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
የህወሓት ደጋፊ የሆነ ሌላ አማጺ ኃይልም ወደ ዋና ከተማዋ እየተጠጋ እንደሆነ አስታውቋል።
በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ተቀላቅለው የሚኖሩባት ዋና ከተማዋ ሌላ ስጋት ተፈጥሮባታል። አንዳንዶች የከተማ አስተዳደሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ የጅምላ እስር እያደረገ ነው ሲሉ ይከሳሉ።
ያም ሆኖ የትግራይ አማጺያን ከከተማዋ ገና በ300 ኪሎ ሜትር ርቀው በኮምቦልቻ ከተማ ነው የሚገኙት።
"አማጺያኑ እንደ ታሊባን አንድም ጥይት ሳይተኮሱ፣ ከተሞችን እየተቆጣጠሩ በግስጋሴ አይደለም እኮ እየመጡ ያሉት…" ብለዋል ቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ቲቦር ናዥ ለቢቢሲ።
"አሁን ህወሓት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች እንኳን ከፍተኛ የመከላከል ጦርነት አለ። አዲስ አበባም (ከገቡ) ደም አፋሳሽ ጦርነት ሊኖር ይችላል" ሲሉ ነገሩ እንደሚባለው እንዳልሆነ አብራርተዋል።
ዋና ከተማዋን መቆጣጠር ልክ የኑክሌየር መሣሪያ ታጣቂዎች ያንን መሣሪያ ለመጠቀም እንደሚዝቱት ዓይነት ስሜት አለው ሲሉ አምባሳደሩ ሁኔታውን አብራርተዋል።
ህወሓት በበኩሉ የሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲደርስ ማድረግ ነው ዋናው ፍላጎቴ ይላል።
"ወደ አዲስ አበባ እንገሰግሳልን። ነገር ግን ጉዳያችን ከአዲስ አበባን አይደለም። የኛ ፍላጎት ዐቢይ በትግራይ ላይ የጣለውን ከበባ እንዲያነሳ ማስገደድ ነው" ብለው ነበር አቶ ጌታቸው ረዳ ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ በቅርቡ በሰጡት ቃለ ምልልስ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ህወሓትን ሽብርተኛ በሚል ፈርጆታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው ይህን ድርጅት እስከመጨረሻው ለመፋለም ዝተዋል፡፡
"ይህን ጠላት በደምና በአጥንታችን ቀብረን የኢትዮጵያን ትንሳኤ በድጋሚ እናበስራለን" ብለዋል፣ በቅርቡ።
የሰላም ንግግሮች የት ደርሰዋል?
አሳሳቢው ሁኔታ ይህ ጦርነት አዲስ ምዕራፍ ውስጥ እየገባ መምጣቱ ነው። ከዚህ ወዲህ ሁለቱም ወገኖች ወደኋላ መመለስ የማይችሉበት ደረጃ ሊደርሱ ይመስላል።
ሌላው ስጋት ደግሞ ጦርነቱ ከኢትዮጵያ ባሻገር ሊስፋፋ ይችላል የሚለው ነው።
ህወሓት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር እንዲንኮታኮት ከሚፈልጉ ሌሎች ኃይሎች ጋር ጥምረት መፍጠር ጀምሯል።
በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ፣ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን አባሳንጆ ጠባብ ቢሆንም የድርድር ዕድል እንዳለ ጠቅሰዋል።
ከሁለቱ ተዋጊ ወገኖች ጋር የተነጋገሩት ኦባሳንጆ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እንደተናገሩት "አሁን ጣልቃ ለመግባት ጊዜው አጭር ነው" ብለዋል።
ኦባሳንጆ ንግግር እንዲጀመርና ችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈለግለት ጥሪ አቅርበዋል። ይሁንና ይህ እንዴት መሳካት እንደሚችል ያሉት ነገር የለም።
በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ለዚህ የተሰጠው ምላሽ ግን አደራዳሪዎች ወደፊት የሚገጥማቸውን ፈተና ፍንትው አድርጎ ያሳየ ይመስላል።
አምባሳደር ታዬ፣ ለንግግር የተደረገውን ጥሪ እንደሚያከብሩ ከተናገሩ በበኋላ ህወሓትን "ወንጀለኛው ቡድን" ሲሉ ነበር የጠቀሱት።
የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው "አብዛኛዎቹ የሰላም ተነሳሽነቶች ሁነኛውን የፖለቲካ ችግር ዋና አጀንዳ ከማድረግ ይልቅ ዐቢይን ለማዳን ያለሙ ናቸው" ሲሉ ተችተዋል።
የአሜሪካው ዲፕሎማት ቲቦር ናዥ፣ ሁለቱን ተዋጊ ወገኖች ለንግግር እንዲቀመጡ የማድረጊያው መንገድ አሜሪና ቻይና እንዲሁም ቱርክን የመሰሉ ሌሎች አገሮች በጋራ ሲሠሩ ነው ብለው ያምናሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "አሜሪካና ቻይና ተመሳሳይ ነገር የሚሉት ከሆነ ከዚያ ሊወጣ አይችልም" ይላሉ አምባሳደር ናዥ።
"ሆኖም መቅደም ያለበት የተኩስ ማቆም ስምምነት ተደርጎ እርዳታ የሚደርስበት ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ከዚያ ቀስ በቀስ የፖለቲካ መፍትሄዎችን ማሰብ ነው።"
የጦርነቱ መነሻ ምንድነው?
ጦርነቱ የጀመረው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና በህወሓት መካከል በተፈጠረ ልዩነት ነው።
ህወሓት ትግራይን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለ27 ዓመታት በበላይነት ሲዘውር የኖረ ፖለቲካዊ ድርጅት ነው።
ዐቢይ ወደ ሥልጣን የመጡት በ2018 ሲሆን ይህም በኦሮሚያ ተከስተው በነበሩ የሕዝብ አመጾችን ተከትሎ በተደረገ ለውጥ ነበር መንበሩን የተቆናጠጡት።
ኦሮሞ በኢትዮጵያ ትልቁ ብሔር ነው። ዐቢይም ከዚሁ ብሔር የተገኙ ሰው ናቸው። በመሆኑም አገሪቱ የገጠማትን ፈተና ለመፍታት ተመራጭ መሪ ሆነው ታይተው ነበር።
ሥልጣን ከያዙ በኋላ ባደረጓቸው ተከታታይ ለውጦች የፖለቲካ ነጻነትን በመፍቀድ ከኤርትራ ጋር ሰላም ንግግርን በመጀመር ተወድሰዋል።
ከኤርትራ ጋር የጀመሩት ሰላም ጥረት ግን ህወሓትን ገሸሽ ያደረገ ስለነበረ በህወሓትና በዐቢይ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን መቃቃር ከፍ ወዳለ ደረጃ አደረሰው።
ይህ ውጥረት ባለበት ሁኔታ የህወሓት ኃይል በሰሜን የመከላከያ ዕዝ ላይ ሰነዘረ በተባለው ጥቃት የተነሳ የፌዴራል መንግሥት ጦርነት አወጀ።
ይህም ጦርነት እስከዛሬ ቀጥሏል።