ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ ፌስቡክና ቴሌግራምን ጨምሮ የማኅበራዊ ሚዲያዎች አገልግሎት ተቋረጠ
የብሔራዊ ፈተና ጥያቄዎች በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ሲዘዋወሩ ነበር ተብሎ ከተነገረ በኋላ በኢትዮጵያ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ዋትስአፕ እና ኢንስታግራም አገልግሎታቸው ተቋረጠ።
የኢንተርኔት ዕቀባዎችን የሚከታተለው ኔትብሎክስ ባወጣው መረጃ ከሰኞ ጥቅምት 29/2014 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ አንስቶ በኢትዮጵያ የፌስቡክ እና የፌስቡክ ሜሴንጀር አገልግሎቶች መቋረጥ እንደገጠማቸው ማረጋገጡን ገልጿል።
ጨምሮም መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ ከሁለቱ የማኅበራዊ ሚዲያ መገልገያዎች በተጨማሪ በአገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪው ኢትዮቴሌኮም ሰርቨር ላይ የዋትስአፕ እና የቴሌግራም የመልዕክት መለዋወጫ መድረኮች ተቋርጠዋል ብሏል።
ቢቢሲ በአዲስ አበባ ካሉ የማኅበራዊ መገናኛ መድረክ ተጠቃሚዎች ለማጣራት እንደሞከረው የተጠቀሱትን የማኅበራዊ መገናኛ መድረኮችን በቀጥታ መጠቀም እንደማይቻልና ቪፒኤን የተባለውን መንገድ እየተከተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት የሁለተኛ ደረጃ አገር አቀፍ ፈተናዎች በሚሰጡበት ጊዜ ኩረጃንና ሐሰተኛ የመልስ ልውውጥን ለመከላከል በሚል የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎቶች ተዘግተው የነበሩባቸው አጋጣሚዎች አሉ።
ሰኞ ዕለት የአገር አቀፍ ብሔራዊ ፈተና መጀመርን ተከትሎ አንዳንድ የመንግሥት ተቃዋሚዎች የፈተናው የጥያቄ ወረቀት ቅጂዎች ናቸው ያሏቸውን ፎቶዎች እንዲሁም የመልስ ዝርዝሮችን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲያሰራጩ ነበር።
ነገር ግን የአገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር እየተሰጠ ካለው ፈተና ላይ ምንም አይነት ጥያቄም ሆነ መልስ እንዳልወጣና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሰራጩ ያሉት ሐሰተኛ መሆናቸውን ገልጿል።