ከሶዶ እስከ ሚሽገን፡ የማጂ ኃይለማርያም (ዶ/ር) የአእምሮ ጤና አስተዋጽኦ ጉዞ

"እዚህ ለምን መጣሽ?" ተብዬ ስጠየቅ "አሜሪካ የምኖር አፍሪካዊ ባለሙያ ነኝ። እናንተ አገር ካሉ ድሃ እና አገልግሎቶች በአግባቡ ያልደረሷቸው ሰዎች ጋር እሠራለሁ። ልክ የእናንተ ፒስ ኮር አባላት ከአሜሪካ ውጪ እንደሚያደርጉት" ብዬ መልስ እሰጣለሁ። ይህን ካልኩ በኋላ ጠያቂዎቹ ወይ ይደነግጣሉ አልያም ምቾች የሚነሳ ዝምታ ይከተላል።

ጽሑፉ የተወሰደው ከማጂ ኃይለማርያም (ዶ/ር) የትዊተር ገጽ ነው። 'ፒን' [ቀድሞ እንዲታይ] አድርጋዋለች። አሜሪካ ውስጥ የምትሠራውን እና አመለካከቷን ያንጸባርቃል።

ጥቁሮችን ሁሌም እንደ 'እርዳታ ጠባቂ'፣ ነጮችን ደግሞ ሁሌም እንደ 'አዳኝ' የሚስለውን የተዛባ አመለካከት የሚሰብር አቋም ነው።

እአአ 2016 አካባቢ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ከሄደች በኋላ ኒው ዮርክ፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ፊላዴልፊያ ቆይታለች። ከዚያም አሁን ወደምትኖርበት ሚሽገን አቀናች።

በጉዞዋ ያስተዋለችው ስለ አሜሪካ ብዙም የማይነገረውን ገጽታ ነው። ድህነትን። በዜና ወይም በፊልም የሚታየው የጥቁር እና የቡናማ ሕዝቦች ድህነት ብቻ ነው። ድህነት ግን ቀለም የለውም። ድንበር የለውም።

ዶ/ር ማጂ ያየችውም ይህንን እውነታ ነው። ሚሽገን ውስጥ በድህነት የሚኖር ሕዝብ አለ፣ ከአምስት ሕፃናት አንዱ የረሃብ ተጠቂ የሆነባቸው አካባቢዎች አሉ፣ የወንጀል መጠን ከፍተኛ ነው፣ አማካይ በሕይወት የመቆየት እድሜ 65 የደረሰባቸው ቦታዎች አሉ፣ እኩልነትም አልሰፈነም።

"ስለ ሕብረተሰቡ የሰማኋቸው አንዳንድ ነገሮች አስደንጋጭ ናቸው። ስለእነዚህ ነገሮች በዜናም አንሰማም በፊልም አናይም" ትላለች።

ይህንን የማኅበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ ስትሠራ ግን እንዴት ጥቁር፣ ስደተኛ፣ ሴት ይህንን ማድረግ ትችላለች? ብሎ የሚጠይቅ አልጠፋም።

"ጥቁር ስትሆኚ ስደተኛ ነሽ፤ ጥቁር ስትሆኚ አገርሽ ተቸግራ ነው አሜሪካ የመጣሽው እንጂ፣ እዚህ ያለውን ሰው ለመርዳት ከእነሱ እኩል እንደምትሠሪ ማሰብ አይፈልጉም።"

በትዊተር ገጿ 'ፒን' ያደረገችው ጽሑፍ ይህንን ስሜቷን የሚገልጽ ነው።

በሚሽገን ስቴት ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ናት። የአእምሮ ጤና ዋነኛ ትኩረቷ ነው። ሴቶች፣ የሕግ ታራሚዎች እና አቅመ ደካሞችን የተመለከቱ ጥናቶች አሏት።

በኢትዮጵያም በአሜሪካም ያሉ አገልግሎቶች በአግባቡ ያልደረሷቸው ሰዎችን [Underserved Communities] ለመርዳት ትሠራለች።

በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ ያሉት ችግሮች መካከል ሰፊ ልዩነት ቢኖርም፤ በየትኛውም አገር አገልግሎት (ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ) ያልደረሳቸው ዜጎች የሚገጥሟቸው ፈተናዎች ተቀራራቢ ናቸው።

"በኢትዮጵያ የሠራሁት ሥራ አሜሪካ ውስጥ ለምሠራው አዘጋጅቶኛል" የምትለውም ለዚህ ነው።

የአእምሮ ሕክምና ተደራሽነት ከጾታ እና ገቢ አንጻር

በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሕክምና አገልግሎት የሚደርሳቸው ሰዎች ቁጥር ከከተሜው አንጻር ያነሰ ነው። የአእምሮ ሕክምና ሲሆን ደግሞ ቁጥሩ በእጅጉ ያሽቆለቁላል።

ዶ/ር ማጂ ከስምንት ዓመት በፊት በደቡብ ክልል የሠራችው ጥናት የአእምሮ ሕክምና ተደራሽነትን በቀዳሚነት ከጾታ እና ከገቢ አንጻር ይቃኛል።

እሷን ጨምሮ 10 የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች 'ፕራይም' በሚባል ፕሮጀክት ሥር ነበሩ። የፕሮጀክቱ አላማ በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት ውስጥ የአእምሮ ሕክምናን ተደራሽ ማድረግ ነው።

የፕሮጀክቱ ተሳታፊዎች ከጤና ሚኒስትር፣ ከዞን እና ከወረዳ የጤና ቢሮ፣ ከፖሊሲ አውጪዎች፣ ከማኅበረሰብ አባላት እና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ይገናኙ ነበር።

የዛሬ ስምንት ዓመት በጉራጌ ዞን፣ በሶዶ ወረዳ፣ ቡኢ ከተማ ውስጥ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ጣቢያዎች አንድም የአእምሮ ሕክምና ማዕከል እንዳልነበረ ታስታውሳለች።

በወቅቱ ስምንት የጤና ጣቢያዎች ነበሩ። አንዳቸውም ግን የአእምሮ ሕክምና አቅርቦት አልነበራቸውም። የዶ/ር ማጂ ንቅናቄ በጤና ጣቢያዎቹ የአእምሮ ሕክምና ማዕከላት እንዲከፈቱ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ሠልጥነው የአእምሮ ሕክምና እንዲሰጡም ነበር።

በሂደት በመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መስጫዎች የአእምሮ ሕክምና ማዕከላትን ማካተት ተችሏል።

"አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቹ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የአእምሮ ጤና አገልግሎት እየሰጡ ነው። የዛሬ ስምንት ዓመት ስንጀምር ከነበረው አሁን ነገሮች እየተስተካከሉ ነው። አሁንም ግን ብዙ ይቀራል" ትላለች።

የአእምሮ ጤና ማዕከላት ቢኖሩም በዋነኛነት አቅመ ደካሞች እና ሴቶች ምን ያህል ይገለገላሉ? የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው።

ስለ አእምሮ ጤና ያለው የተዛባ አመለካከት፣ የሕክምና ወጪን መሸፈን አለመቻል፣ የመጓጓዣ ውስንነት እና ሌሎችም ብዙ መሰናክሎች ይስተዋላሉ።

የዶ/ር ማጂ ጥያቄዎች፤ ሴቶች እና ወንዶች እኩል ጤና ጣቢያ ሄደው ይታከማሉ? ድሆች እና ሀብታሞችስ? የሚሉት ናቸው።

በሌላ በኩል ሕክምና ጀምረው የሚያቋርጡም ብዙ ናቸው። ለዚህ ምክንያቱ የአእምሮ ጤና እንደ ሌሎች የሕክምና አይነቶች ድጋፍ ስለማይደረለት ነው።

ዶ/ር ማጂ እንደ ምሳሌ የምትጠቅሰው ቲቢ እና ኤችአይቪን ነው።

"የኤችአይቪ እና ቲቢ ሕሙማንን የሚደግፍ፣ ክትትል የሚያደርጋላቸው፣ መድኃኒታቸውን የሚያሟላላቸው አሠራር አለ። የአእምሮ ጤና ላይ ግን አብዛኛው ወጪ የሚሸፈነው በግለሰቦች ወይም በቤተሰቦቻቸው ነው።"

በርካታ አእምሮ ሕሙማን ወደ ሕክምና እንደማይሄዱ እና ሕክምናውን ከጀመሩ በኋላ እንደሚያቋርጡም ጥናቷ ይጠቁማል። ለሕሙማን የሚሰጡ መድኃኒቶች ያላቸውን ከባድ የጎንዮሽ ጉዳት መቋቋም አቅቷቸው መድኃኒት የሚያቋርጡም አሉ።

"ሰው ባንዴ ታክሞ፣ መድኃኒት ወስዶ መዳን ነው የሚፈልገው እንጂ ለረዥም ጊዜ የጤና ተቋም አይሄድም። ረዥም ጊዜ የሚወስድ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች የሚደግፍ አሠራርም የለም።"

በዶ/ር ማጂ ዕይታ የአእምሮ ሕክምናን እንደ ጤና ጣቢያ እና ጤና ኬላ ባሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መስጫዎች ማካተት አንዱ መፍትሔ ነው።

ሌላው የአእምሮ ሕክምና የሚያስፈልገውን ጊዜ እና ወጪ ከግምት ያስገባ አገር አቀፍ አሠራር መዘርጋት ነው።

በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ተኝቶ ሕክምና ማግኘት የሚቻለው በአማኑኤል የአእምሮ ጤና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ መሆኑ ክፍተት ፈጥሯል።

ከጋምቤላ፣ ከደቡብ ኦሞ ወዘተ አማኑኤል ድረስ የሚሄዱ ሕሙማን ይጉላላሉ። ታክሲ አልጭናችሁም ይላቸዋል ወይም የአእምሮ ሕመምተኛ መሆናቸውን ሲያውቅ ዋጋ ይጨምርባቸዋል። የማረፊያ ሆቴል ወጪም ሌላ እራስ ምታት ይሆናል።

"መፍትሔው የሕክምና አገልግሎቱን እዚያው በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ማድረግ ነው። በዚህ መንገድ ቶሎ ይታከማሉ፣ ሕይወታቸው ቀና ይሆናል፣ ሥራ መሥራትም ይችላሉ" ስትል ታስረዳለች።

በሶዶ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የአእምሮ ጤና ማዕከላት ከተከፈቱ ወዲህ ሳይታከሙ የሚቀሩ የአእምሮ ሕመሞች ቁጥር በአንጻራዊነት እንደቀነሰ ትናገራለች።

ከ90 በመቶ በላይ ሳይታከሙ የሚቀሩ የአእምሮ ሕሙማን ቁጥር ወደ 81 በመቶ ዝቅ ማለቱም ተስፋ ይሰጣታል።

ነጻ የስልክ መስመር

'ሆት ላይን ፎር ኢቲ' [Hotline for ET] የተባለ የአእምሮ ጤና ነጻ የስልክ መስመር እንዲጀመር ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ፊርማ ማሰባሰብ ጀምራለች።

952 ነጻ የስልክ መስመር የጤና መረጃ ቢሰጥም፤ የአእምሮ ጤና እራሱን የቻለ የጥሪ መስመር እንደሚያስፈልገው ታምናለች።

"እራስን የማጥፋት አዝማሚያ ያለው ሰው ደውሎ የሚነጋገርበት መስመር የለም። ሰው ቀውስ ሲገጥመው፣ ጥያቄ ሲኖረው፣ ባለሙያ መድረስ ሳይችል ሲቀር ድጋፍ የሚሰጥ ነጻ የስልክ መስመር ያስፈልጋል።"

ምሥራቅ አፍሪካን ጨምሮ በሌሎችም የዓለም ክፍሎች ከአንድ በላይ የአእምሮ ጤና ድጋፍ ሰጪ ነጻ የስልክ መስመሮች አሉ።

የጤና ሚንስትር ከ952 ነጻ የስልክ መስመር የተወሰነው ለአእምሮ ጤና ድጋፍ እንዲውል ቢስማማም፤ ሆትላየን ለማድረግ የኢትዮ ቴሌኮም ይሁንታ እንደሚያስፈልግ ትገልጻለች። አሁን ከቴሌ ጋር ንግግር ጀምረዋል።

የአእምሮ ሕመም የገጠመው ሰው 952 ደውሎ የሚያገኘው ኦፕሬተር በቀጥታ የሚረዳው እንጂ "አንድን ይጫኑ፣ ሁለትን ይጫኑ" የሚሉ አማራጮች የሚያቀርብ መሆን የለበትም።

ዶ/ር ማጂ፤ የአእምሮ ጤና ነጻ የስልክ መስመር አስፈላጊነትን የምትገልጸው "ቀውስ ላይ ያለ ሰው የሚቃጠል ቤት ውስጥ እንዳለ ሰው ነው። አማራጮች ሳይሆን በቀጥታ እርዳታ ማግኘት አለበት" በማለት ነው።

የነጻ የስልክ መስመር አስፈላጊነት እንዲታወቅ በማኅበራዊ ሚዲያ ከሙያ አጋሮቿ ጋር ንቅናቄ እያደረጉ ይገኛሉ። ጉዳዩ በሰዎች ዓይን እንዲገባ፣ ሌሎች ባለሙያዎች እንዲሳተፉ እና ውሳኔ ሰጪዎችን ለማሳመንም እንደሚረዳ ታምናለች።

የአቻ አገልግሎት

ድባቴ [Depression]፣ በተለዋዋጭ ተቃራኒ ስሜቶች መዋጥ [Bipolar Disorder]፣ ሐሳብ እና ባሕሪን የሚያዛባ የእውነታ መንጋደድ [Schizophrenia] ከዶ/ር ማጂ የጥናት ትኩረቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

በኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት በተለያየ ሕመም ምክንያት ወደ ሕክምና የሚሄዱ ሰዎችን የአእምሮ ጤና መመርመር [Screening] አለመለመዱን ትተቻለች።

ለምሳሌ አሜሪካ ውስጥ እርጉዝ እናቶች ወይም ለረዥም ጊዜ በሕክምና የቆዩ የድባቴ ምርመራ ይደረግላቸዋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የሥነ ልቦና ማማከር አገልግሎት ተደራሽነት ውስን ከመሆኑም በላይ ዋጋው አይቀመስም።

መድኃኒት የማያስፈልጋቸው የአእምሮ ሕክምናዎችን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ የአቻ አገልግሎትን [Peer Provided Service] ዶ/ር ማጂ ትመክራለች።

የአቻ አገልግሎት፤ የአንድ ማኅበረሰብ አባላት እርስ በእርስ የሚደጋገፉበት አሠራር ነው። የተወሰኑ ሰዎች መሠረታዊ የአእምሮ ጤና ድጋፍ በባለሙያዎች ከተማሩ በኋላ በማኅበረሰቡ ውስጥ ችግሮችን ለመፍታት ይሞክራሉ።

"ከኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር አንጻር በሁሉም አካባቢ ባለሙያዎች ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ድባቴ እና እራስን የማጥፋት አዝማሚያን ለመቀነስ አንዱ መንገድ ሰዎች በአጭር ጊዜ ሙያውን ተምረው በእነሱ ደረጃ ያሉ ሌሎች ሰዎችን የሚረዱበትን መንገድ መዘርጋት ነው።"

ዚምባብዌን እንደ ምሳሌ ብንወስድ የአግዳሚ ወንበር ምክክር [Friendship Bench] የሚባል አሠራር አለ። አያቶች ወይም እናቶች ተመርጠው አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጠው ሰዎች ያነጋግራሉ። ድባቴ የያዛቸውን ምክር [Intervention] ይሰጣሉ። ይህም ኤችአይቪ የያዛቸው ሴቶችንም ያካትታል።

የታራሚዎች የአእምሮ ጤና

ዶ/ር ማጂ "በጣም ለልቤ ቅርብ የሆነ" የምትለው የአሜሪካ ታራሚዎች የአእምሮ ሕመም ጥናትን ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት ከሚሽገን ስቴት ዩኒቨርስቲ እና ከሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች አጥኚዎች ጋር በአሜሪካ መንግሥት ብሔራዊ የጤና ተቋም አማካይነት 1.5 ሚሊዮን ዶላር የጥናት ማስኬጃ አሸንፋ ነው የተሠራው።

እስር ቤት ካሉት 60 በመቶው አንድ ወይም ከዚያ በላይ የአእምሮ ሕመም አለባቸው። ታራሚዎቹ ተፈትተው ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ ምን ድጋፍ ይደረግላቸዋል? የሰዎቹን የአእምሮ ጤናስ እንዴት ያሻሽላል? የሚሉት የጥናቱ ትኩረት ናቸው።

መታሰር ከሰው ይነጥላል። ማኅበራዊ ድጋፍ ያሳሳል። ከማኅበራዊ አገልግሎቶችም ያርቃል።

የዶ/ር ማጂ ምክረ ሐሳብ፤ የአእምሮ ታማሚ ታራሚዎች ከእስር ሲለቀቁ ልክ እንደእነሱው ካሉ የቀድሞ ታራሚዎች ጋር ተገናኝተው የአቻ ድጋፍ እንዲያገኙ ማስቻል ነው።

"ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው እና በሂደቱ ያለፉ ሰዎች ቢደግፏቸው በድጋሚ መታመም [Relapse] እና በሆስፒታል አልጋ መያዝ ይቀንሳል።"

በሙከራ ደረጃ ያለው ሐሳቡ ውጤታማ ከሆነ በአሜሪካ አገር አቀፍ ደረጃ ይተገበራል ብላ ትጠብቃለች።

የቅርብ አጋር ጥቃት

ሌላው ጥናቷ እርጉዝ እናቶች ወይም ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ያሏቸው እናቶች ከቅርብ አጋራቸው የሚደርስባቸውን ጥቃት [Intimate Partner Vioence] ይመለከታል።

በባለቤት፣ በእጮኛ ወይም በወንድ ጓደኛ የሚደርሰው ጥቃት ብዙ ጊዜ ከአእምሮ ጤና ጋር እንደሚገናኝ ታስረዳለች።

እናቶች እና እርጉዝ ሴቶች በቅርብ አጋር ጥቃት ሳቢያ ለድባቴ እንዲሁም ከሰቆቃ በኋላ ለሚገጥም የሥነ ልቦና ውጥረት [PTSD] ይጋለጣሉ።

የእሷ ሐሳብ፤ ከማኅበረሰቡ እናቶችን መርጦ በማሠልጠን ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ከእናቶቹ ጋር ጓደኛ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

"እናቶቹ [Interpersonal Psychotherapy] ሠልጥነው በችግሩ ውስጥ እያለፉ ላሉ ሴቶች፣ ድባቴ ለገጠማቸው ሴቶች እና ከቅርብ አጋር ጥቃት ለተረፉ ሴቶች ምክር ይሰጣሉ።"

የዚህ አሠራር ግብ፤ ሴቶች ከጥቃት ነጻ የሚሆኑበትን መንገድ መቀየስ፣ በተደጋጋሚ ለቅርብ አጋር ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ የሚጠብቅ የደኅንነት መዋቅር መመሥረት፣ ድባቴን መቀነስ እና ከሰቆቃ በኋላ የሚገጥም የሥነ ልቦና ውጥረትን ማርገብ ነው።

በሙከራ ደረጃ ያለው ሐሳቡ ውጤታማ ከሆነ በአሜሪካ በአገር አቀፍ ደረጃ ይተገበራል ብላ ትጠብቃለች።

ዶ/ር ማጂ ከየት ወደ የት. . .

የመንግሥት ሠራተኛ ቤተሰብ የመጀመሪያ ልጅ ናት። ከሦስት ታናናሾቿ ጋር "በርቱ! ተማሩ!" እየተባሉ ነው ያደጉት።

ልጅ ሳለች ስታድግ ፖለቲከኛ የምትሆን ይመስላት ነበር። "ሥልጣን ይዤ የዚችን አገር ችግር በአንዴ የምፈታ ነበር የሚመስለኝ" ስትል ታስታውሳለች።

በ18 ዓመቷ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስትገባ ግን "የፖለቲካውን ጉድ አየሁት" ትላለች። በአንዴ ፖለቲከኛ ሆኖ የኢትዮጵያን ችግር የመቅረፍ ሕልሟም ተነነ።

ዩኒቨርስቲ ስትገባ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት በትንሹ መጀመር አለብኝ የሚል አቋም ያዘች።

"ከግለሰቦች፣ ከቤተሰቦች እና አገልግሎት ካልደረሳቸው ማኅበረሰቦች ጋር ብሠራ፤ የምፈልገውን ለውጥ በተወሰነ ደረጃ ማየት እችላለሁ" ብላ ተነሳች።

የመጀመሪያ ዲግሪ ፍልስፍና፣ ሁለተኛ ዲግሪ የማኅበረሰብ ሥራ [Social work] ተማረች።

ያኔ አማኑኤል የአእምሮ ጤና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጥናት ልትሠራ ስትሄድ "በኢትዮጵያ ስላለው የአእምሮ ጤና ችግር ዓይኔ ተገለጠ" ትላለች። ከዚያን ጊዜ ወዲህም በዋነኛነት የአእምሮ ጤና ላይ በመሥራት ገፍታለች።

ዶ/ር ማጂ በጣም የምትኮራበት ሥራ በሶዶ በመጀመሪያ ሕክምና መስጫ ተቋሞች የአእምሮ ሕክምና ማዕከላት የተከፈቱበትን ፕሮጀክት ነው።

"ሰዎች በመጀመሪያው ቀጠሮ መጥተው መድኃኒታቸውን ሲውጡ አይቻለሁ። ቁጭ ብዬ ያዋራኋቸሁ ቤተሰቦች ያሳዩትን ለውጥ ሰምቻለሁ። በመጀመሪያ ሕክምና መስጫ ደረጃ የአእምሮ ሕክምና እንዲካተት ንቅናቄ ማድረጌ ልክ ነበር እንድል አድርጎኛል" ትላለች።

በአሜሪካ፣ በሚሽገን ግዛት፣ በፍሊንት ከተማ የሴቶች አቅም ማጎልበቻ ማዕከል እንዲቋቋም ምክንያት የሆነ ጥናት ላይ መሳተፏ ሌላው ስኬቴ የምትለው ነው።

ዶ/ር ማጂ የወደፊት ዕቅዷ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካም ያሉ አገልግሎት ያልደረሷቸው ማኅበረሰቦችን በመርዳት መቀጠል እንደሆነ ትናገራለች።

"አሜሪካ ከፍተኛ ገቢ ያላት አገር ሆና ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማኅበረሰብ አላት። በኢትዮጵያ ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማኅበረሰብ ቁጥር ያመዝናል። ኢትዮጵያ ያሉት እዚህ አሜሪካ ካለው ተሞክሮ እንዲማሩ እዚህም 'እኛ አሜሪካዊ ነን' ሳይሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ውጤታማ ከሆኑ መንገዶች እንዲማሩ የመሥራት ዕቅድ አለኝ።"