ፌልትማን ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ጋር ተወያዩ

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፈሪ ፌልትማን እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ።

የፎቶው ባለመብት, @AUC_MoussaFaki

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፈሪ ፌልትማን እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ።

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፈሪ ፌልትማን ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ጋር ተወያዩ።

ሙሳ ፋኪ ከአምባሳደሩ ጋር በወቅታዊ የኢትዮጵያ እና ሱዳን ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።

ኮሚሽነሩ ከጄፈሪ ፌልትማን ጋር ከብሔራዊ እና አህጉራዊ አካላታት ጋር በመሆን ውይይት እና ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማምጣት ልናደርግ የምንችለውን ጥረት በተመለከተ ተነጋግረናል ብለዋል።

ዛሬ እኩለ ቀን አዲስ አበባ የገቡት ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት እየተባባሰ ለመጣው ጦርነት መላ ለመሻት እንደሆነ በስፋት ተዘግቧል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንዳለው የጦርነቱ መጠነ ሰፊነት አሁን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ደሴና ኮምቦልቻን መቆጣጠራቸው የተነገረላቸው የትግራይ ኃይሎች ትናንት ከሚሴ ከተማን መቆጣጠራቸውን ይፋ አድርገዋል።

መንግሥት በዚህ ረገድ ያለው ነገር የለም። ከሚሴ ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በሰሜን አቅጣጫ 330 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኝ ናት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንትና የጦርነቱ አንደኛ ዓመትና የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ጥቃት የደረሰበትን ዕለት ለመዘከር በነበረ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር "…ይበልጡኑ ጉድጓድ በጥልቀት እየቆፈረ ይገኛል። ይህ በጥልቀት የሚቆፍረው ጉድጓድ ጠላት የሚቀበርበት እንጂ ኢትዮጵያ የምትፈርስበት አይሆንም። ይህንን ጠላት በደማችን፣ በአጥንታችን ቀብረን የኢትዮጵያን ክብር ቀና እናደርጋለን" ሲሉ ተደምጠዋል።

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ወዳጅ አገራት ከዕለት ዕለት እየተባባሰ የመጣውን ጦርነት አሳሳቢነት በማስተጋባት ላይ ናቸው።

አሜሪካ በበኩሏ ንግግር እንዲጀመር የዲፕሎማቲክ ጥረቷን አጠናክራ ቀጥላለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን ገልጠው ለድርድር የሚሆን ማንኛውንም ድጋፍ እንደሚሰጡ እንደገለጡላቸው ጉተሬዝ በትዊተር ሰሌዳቸው ጽፈዋል።

ይሁን እንጂ ሁለቱም ተዋጊ ወገኖች የድርድር ሐሳብን ገሸሽ ያደረጉት ይመስላሉ።

በጦር ሜዳ የበላይነት ማግኘታቸውን የሚናገሩት የትግራይ ኃይሎች 'በውድቀት አፋፍ' ላይ ነው የሚገኘው ከሚሉት መንግሥት ጋር ንግግር መጀመር አስፈላጊ እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላ አገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማወጁን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለትግል እንዲነሳ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ለሚገኙ ደግሞ እንዲታጠቁና አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ ከ7ሚሊዮን ሕዝብ በላይ አስቸኳይ የምግብ እርዳታን እንደሚሻ ይፋ አድርጓል፡፡በትግራይ ክልል ብቻ 400 ሺህ የሚሆን ሕዝብ ለከፋ ረሀብ-መሰል አደጋ መጋለጡ ተወስቷል፡፡

ሆኖም የተራድኦ ድርጅቶች በአካባቢው ያለው ጦርነትና የመንግሥት ገደብ ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ ፈታኝ እንዳደረገባቸው ይናገራሉ፡፡