ፕሬዚዳንት ባይደን የሱዳን የሲቪል አገዛዝ በአስቸኳይ እንዲመለስ አሳሰቡ

የሱዳን ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የሱዳን ወታደራዊ መሪዎች የሲቪል አገዛዙን በአስቸኳይ እንዲመልሱ እና ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ አሳስበዋል።

በጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን የተመራውን መፈንቅለ መንግስት በመቃወም አደባባይ ላይ የወጡ ሰልፈኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እንዲቆምም ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል።

"ለሱዳን ወታደራዊ ባለስልጣናት የምናስተላልፈው መልእክት በርካታ እና ግልፅ ነው። የሱዳን ህዝብ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን እንዲያሰማ እና በሲቪል የሚመራ የሽግግር መንግስት ወደነበረበት መመለስ አለበት" ሲሉም በመግለጫቸው አስተላልፈዋል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሱዳንን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በመቃወም የአረብ ሊግ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ የአለም አቀፍ ማህበረሰቡን ውግዘት ተቀላቅለዋል።

በሱዳን በቅርብ ጊዜ የተከሰቱት ክስተቶች ሃገሪቷን በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ኋላ የሚጎትቱ ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንት ባይደን ነገር ግን "የሱዳንን አብዮት አላማ ለማራመድ ከሱዳን ህዝብ እና ከሰላማዊ ትግል ጋር እንቆማለን" በማለት የመንግሥታቸውን አቋም ገልጸዋል።

በተቃውሞው የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 11 መድረሱንም የህክምና ምንጮች ገልጸዋል።

በአውሮፓውያኑ 2019 ለአስርት ዓመታት ሱዳንን አንቀጥቀው የገዙት ኦማር አልበሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በሲቪል መሪዎች እና በወታደራዊ አቻዎቻቸው መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል።

በሲቪል እና በወታደራዊ መሪዎች መካከል የተደረገው የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት ሱዳንን ወደ ዲሞክራሲ ለመምራት የተነደፈ ቢሆንም ከባለፈው አንድ ወር በፊት የተደረጉ በርካታ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ግን በተፃራሪው አገሪቷ በተቃራኒው አቅጣጫ እየሄደች እንደሆነ ያመላከተ ነው።

የስልጣን መጋራት ምክር ቤት መሪ የነበሩት ጄኔራል ቡርሐን ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመሸጋገር ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀው ምርጫው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2023 ሐምሌ ወር ሊካሄድ እንደታቀደም ተናግረዋል።