በመቀለ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ስድስት ሰዎች ሞቱ - የህክምና ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, AC
በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና መቀለ ላይ በደረሰው የአየር ድብደባ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ ቢያንስ 27 ሰዎች መቁሰላቸውን አንድ ነርስ እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
ለአንድ አመት በዘለቀውና ከትግራይ ዓማፂዎች ጋር እየተካሄደ ያለው ጦርነት የቀጠለ ሲሆን የፌደራል ሃይሎች በከተማዋ ላይ ከአንድ ሳምንት በላይ የአየር ድብደባ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
በመቀለ ዓይደር ሆስፒታል የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት አስተባባሪ ነርስ አበበ ሃፍቱ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት የአየር ጥቃት ያስከተለው መዘዝ "አሰቃቂ" መሆኑን ገልፀው አስከሬናቸው "ተቆራርጠዋል" ብለዋል።
አንዳንድ ሕመምተኞች በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አክለውም "የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል" ብለዋል።
ከ500ሺህ በላይ ህዝብ በሚኖርባት መቀለ ላይ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ይህ ስድስተኛው የአየር ድብደባ ነው።
የመንግሥት ኮምንኬሽን በበኩሉ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ሁለተኛው ክፍል በአየር መደብደቡን አስታውቆ ፤ይህ ተቋም "ህወሓት ወታደራዊ መሣሪያዎችን የሚጠግንበት" እንደሆነ ገልጿል።
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ዛሬ በመቀለ ከተማ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ገልጸው "የአየር መከላከያ ኃይላችን እየተዋጋ ነው" ብለዋል።
ጦርነቱ እንደ አዲስ ተጋግሎ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውጊያ መቀጠሉን ተከትሎ፤ የፌደራሉ መንግሥት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተከታታይ በመቀለ ከተማ የአየር ጥቃት እየተፈጸመ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የአየር ጥቃት የተሰነዘረው በሽብርተኛነት የተፈረጀው ህወሓት ለተለያዩ ወታደራዊ አገልግሎቶች በሚያውላቸው የተመረጡ ኢላማዎች ላይ ነው ቢልም ህወሓትና የመቀለ ሲቪል ነዋሪዎች በበኩላቸው በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ንጹሃን ዜጎች እንዲሁም በነዋሪዎች ሰፈር ላይ ነው የደረሰው ይላሉ።
ቢቢሲ ትግርኛ በአየር ጥቃቱ ቆስላ ወደ አይደር ሆስፒታል የገባችን ሴት ያነጋገረ ሲሆን።

የፎቶው ባለመብት, AC
"ወደ ሆስፒታል እንዴት እንደመጣሁ አላውቅም፣ እራሴን ስቼ ነበር። የአየር ጥቃቱ በደረሰ ጊዜ እኔ ከሁለት ልጆቼ ጋር ቤቴ ውስጥ ነበርኩኝ። አሁን የት እንዳሉ አላውቅም" ብላለች
በግራ እጇ ላይ በድበደባው በደረሰባት አደጋ በሆስፒታል ስትታከም የነበረች ሌላ ሴት "በአካባቢው ምንም አይነት ወታደራዊ ቦታ የለም። የመኖሪያ አካባቢዎችን በአየር ደበደቡ። ቅርፊቱ ቤታችን ላይ ወደቀ፣ ተጎድቻለሁ እና ቤቴ በከፊል ፈርሷል።" ብላለች
"የጎረቤቴ ቤት ሙሉ በሙሉ ወድሟል። በህይወት ያሉ አይመስለኝም።" በማለት አስረድታለች።
ቢቢሲ ትግርኛም በአንድ መኖሪያ አካባቢ በፍርስራሹ እየቆፈሩ አስከሬን የሚፈልጉ ሰዎችን የሚያሳይ ምስል እና ቪዲዮ አግኝቷል።
ሌላ ግለሰብ ለቢቢሲ እንደገለጹት አስከሬኖቹ የሶስት አመት ህጻን ጨምሮ "ንፁሃን ህጻናት" ይገኙበታል።
"አለም ህይወትን ለማዳን እርምጃ መውሰድ አለበት" ሲልም ተናግረዋል።
ቤታቸው የፈረሰባቸው ሌላው ነዋሪ ''ሌሊቱን ሙሉ እየጸለይኩ ነበር፤ ዛሬ ግን ይህ በእኛ ላይ ደረሰ። እግዚአብሔር ግን ሕይወቴን አዳነኝ።" ብለዋል።
ጥቅምት 8/ 2014 ዓ. ም. የአየር ድብደባ ከተፈጸመ በኋላ በቀናት ልዩነት በተደጋጋሚ መቀለ ውስጥ የአየር ጥቃት ተፈጽሟል።
የመጀመሪያው ጥቃት ከመቀለ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ሃሬና ወይም መሰቦ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እና አዲሃቂ ተብሎ በሚጠራው የገበያ አካባቢ መሆኑን የህወሓት አመራሮች ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በበኩሉ ይህ ጥቃት በመቀለ ከተማ በተመረጡ ኢላማዎች እንደተፈጸመ እና ያነጣጠረውም ህወሓት ይጠቀምባቸዋል ባላቸው የመገናኛ አውታሮች እና መሣሪያዎች ላይ መሆኑን ማስታወቁ አይዘነጋም።
ጥቅምት 10/2014 ዓ. ም. የደረሰው የአየር ድብደባ ያነጣጠረው በመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ተቋም ላይ እንደሆነ የዐይን እማኞች ለቢቢሰ መግለጻቸው ይታወሳል።
የመንግሥት የወቅታዊ መረጃ አጣሪ በበኩሉ በየአየር ጥቃቱ ኢላማ የተደረጉት የህወሓት የጦር መሣሪያ ማምረቻ እና መጠገኛ ስፍራዎች ናቸው ብሎ ነበር።
ጥቅምት 11/2014 ዓ. ም. ለሦስተኛ ጊዜ የተፈጸመው የአየር ድብደባ ኢላማ ያደረገው የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ይዞታ የነበረ እና በአሁኑ ጊዜ የህወሓት ኃይሎች የማሰልጠኛ ማዕከል መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጾ ነበር።
ህወሓት በበኩሉ ይህንን የአየር ጥቃት "እንደመከተ" በቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው በኩል አስታውቋል።
ከእነዚህ የአየር ድብደባዎች በኋላ ባሉ ቀናትም የአየር ጥቃት መሰንዘሩ ሲገለጽ ቆይቷል።
በዛሬው ጥቃት ስድስት ሰዎች ሲሞቱ፣ 27 ግለሰቦች ሲቆስሉ ከዚህ ቀደም በነበሩ ጥቃቶች ምን ያህል ሰዎች እንደተጎዱ እስካሁን ግልጽ መረጃ የለም።
ሆኖም በመጀመሪያው ጥቃት ቢያንስ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን እና በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን የዐይን እማኞች ገልጸዋል።
ከዚያ በኋላ በደረሰው የአየር ጥቃት ደግሞ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው አንዲት ነፍሰ ጡር ሴትን ጨምሮ ስምንት ሰዎች የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው የአይደር የሆስፒታል የድንገተኛ ክፍል ኃላፊ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት በትግራይ የተነሳው የፌደራል መንግሥቱ እና የህወሓት ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀጠለ ነው።
ለበርካቶች ሞት፣ ረሃብ እና መፈናቀል የሆነው ጦርነት እንዲቆምና ሁለቱ ወገኖች ወደ ፖለቲካዊ ድርድር እንዲመጡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ማሳደሩን ገፍቶበታል።












