መንግሥት በዛሬው የአየር ጥቃት የህወሓት ወታደራዊ ማሰልጠኛ ዒላማ ሆኗል አለ

መቀለ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዚህ ሳምንት ለአራተኛ ቀን ዛሬ አርብ ጥቅምት 12/2014 ዓ.ም የፌደራሉ መንግሥት አየር ኃይል በትግራይ መዲና መቀለ የአየር ጥቃት ፈጸሙ ተገለጸ።

መንግሥታዊው የአስቸኳይ ጊዜ መረጃ አጣሪ ማዕከል ጥቃቱን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ ለአራተኛ ቀን በመቀለ ከተማ የተፈጸመው የአየር ጥቃት ዒላማ የነበረው የህወሓት ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም ነው ብሏል።

ዒላማ የተደረገው አካባቢ በህወሓት ከመያዙ በፊት የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ማሰልጠኛ ተቋም ሆኖ ያገለግል ነበር ብሏል መረጃ አጣሪው በትዊተር ገጹ።

በአሁኑ ወቅት ግን ይህን ቦታ የህወሓት ቡድን ማሰልጠኛ እና ምልመላ የሚያካሄድበት እንዲሁም የወታደራዊ ዘመቻ ግንኑነት ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ነበር ብሏል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የህወሓት ባለስልጣናት በዚህ ሳምንት ለአራተኛ ቀን በመቀለ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ነግረውኛል ብሏል።

በተመሳሳይ የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ምንጮቹን ጠቅሶ በመቀለ ለአራተኛ ቀን የአየር ጥቃት ተፈጽሟል ሲል ዘግቧል።

የህወሓት ምንጮች የአየር ጥቃቱ ዒላማ ምን እንደነበረ እና የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ያሉት ነገር የለም።

ዛሬ ከተፈጸውም የአየር ጥቃት በተጨማሪ መንግሥት ሰኞ፣ ረቡዕ እና ሐሙስ በመቀለ የአየር ድበደባ ማድረጉ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና በአየር ድብደባው ምክንያት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ አውሮፕላን መቀለ ሳያርፍ መቅረቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አገር ውስጥ የሚገኙ ሁለት የሰብአዊ እርዳታ ተቋማት ምንጮቹን ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፤ ዛሬ መቀለ እንዲያርፍ እቅድ ተይዞለት የነበረ ሰብአዊ እርዳታ የጫነ የመንግሥታቱ ድረጅት አውሮፕላን ማረፍ አልቻለም።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ "የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በረራ ዛሬ ጠዋት ከመቀለ ለመመለስ ተገዷል የሚባለውን ማረጋገጫ መስጠት አልችልም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተመድ ሰብአዊ እርዳታ የያዙ አውሮፕላኖችን ወደ ትግራይ መዲና መቀለ በተከታታይ የሚልክ ሲሆን፤ የአውሮፓ ሕብረትም በተመሳሳይ ሁኔታ የእርዳታ አውሮፕላን ወደ ክልሉ ይልካል።

ዛሬ በመቀለ ከተማ በፌደራል መንግሥት አየር ኃይል በተደረገው የአየር ጥቃት ምክንያት ግን የታቀደው የድርጅቱ የእርዳታ አውሮፕላን ሳያርፍ እንደቀረ ተዘግቧል።

የአማጺው ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ ትናንት ከሰዓት አየር ኃይሉ በመቀለ ጥቃት ለማድረስ ሦስት ጊዜ መሞከሩን ነገር ግን "መመከታቸውን" አስፍረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው አየር ኃይሉ ትናንት በፈጸመው የአየር ድብደባ ዒላማ ያደረገው የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ይዞታ የነበረና በአሁኑ ጊዜ የህወሓት ኃይሎች የማሰልጠኛ ማዕከል መሆኑን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

የኢፌድሪ መከላከያ ሠራዊት ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ደግሞ አየር ኃይሉ ባካሄዳቸው የአየር ድበደባዎች "የመሳሪያ ማከማቻ፣ የጥገና ቦታዎችን፣ ማሰልጠኛዎችን፣ የማዘዣ ጣቢያዎችን እና የሎጂስቲክ የሚያቀርቡና ሃብት የሚያሸሹትን ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ከባድ መሳሪያዎቻቸውን" ማውደሙን ገልጿል።

ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት ከቀናት በፊት መልሶ ካገረሸ በኋላ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ ጥቅምት 08/2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር ኃይል የመጀመሪያውን የአየር ጥቃት መቀለ ውስጥ በሚገኙ ኢላማዎች ላይ ማድረጉን መግለፁ ይታወሳል።

በዚህ በሳምንቱ የመጀመሪያ የአየር ጥቃት ሦስት ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቆ ነበር።

በተመሳሳይ ረቡዕ ጥቅምት 10/2014 ዓ.ም ረፋድ ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙ የሚታወስ ሲሆን የመንግሥት መረጃ ማጣሪያ ማዕከል በሰጠው መግለጫ ጥቃቱ ያነጣጠረው "የህወሓት የጦር መሣሪያ ማምረቻና የጦር ትጥቅ ጥገና ጣቢያዎች" ላይ መሆኑን ገልጿል።

በጥቃቱ መቀለ ከተማ የሚገኘው የመስፍን ኢንደስትሪያል ኢንጂነሪንግ የተባለው ተቋም ላይ ጉዳት መድረሱ የተነገረ ሲሆን ስምንት ሰዎች ላይ የመቁሰል ጉዳት መድረሱን የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አንድ ዓመት ሊሞላው ሁለት ሳምንታት የቀረው ጦርነት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የትግራይ ክልልን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ወደ አማራና አፋር ክልሎች መስፋፋቱ ይታወሳል።