ከአራት ዓመት በፊት ማሊ ውስጥ የታገቱት ኮሎምቢያዊት መነኩሲት ተለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Malian President's office
ከአራት ዓመታት በፊት ማሊ ውስጥ ታፍነው የተወሰዱት ኮሎምቢያዊት መነኩሲት ከእግት ተለቀዋል።
ግሎሪያ ሲሲሊያ ናቫሬዝ በፈረንጆቹ 2017 ነው አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙበት ኮቲያላ ግዛት ታፍነው የተወሰዱት።
ከማሊ ዋና ከተማ ባማኮ 400 ኪሎ ሜትር ከምትርቀው ግዛት የተወሰዱት መነኩሲት ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ መለቀቃቸው መነጋገሪያ ሆኗል።
መነኩሲቷ ሙሉ ቢጫ ልብሳቸውን ለብሰው ከተጠባባቂው የማሊ ፕሬዝደንት አሲሚ ጎይታ ጎን ቆመው የተነሱት ፎቶ ብዙዎች እየተጋሩት ነው።
ግሎሪያ እንዲለቀቁ ለአጋቾቹ ገንዘብ ይከፈል አይከፈል ይፋ አልተደረገም።
ከፕሬዝደንቱ ፅ/ቤት የተለቀቀው መግለጫ እንደሚለው መነኩሲቷ የተለቀቁት የተለያዩ የደህንነት መሥሪያ ቤቶች ለአራት ዓመት ተኩል ጥረት ካደረጉ በኋላ ነው።
መግለጫው አክሎ የመነኩሲት ግሎሪያን "ጥንካሬና ብርታት" አድንቋል።
የባማኮ ሊቀ ጳጳስ ዢን ዜብሮ የመነኩሲቷን መለቀቅ ለጋዜጠኞች አረጋግጠው አሁን "በጥሩ ጤንነት ላይ ናቸው" ብለዋል።
"እህታችን እንዲለቀቁ ብዙ ፀልየናል። የማሊ አስተዳዳሪዎችን እንዲሁም እንድትለቀቅ የረዱንን ሁሉ አመሰግናለሁ።"
ሊቀጳጳሱ ኤኤፍፒ ለተሰኘው የዜና ወኪል እንደተናገሩት መነኩሲቷ ወደ ሮም ይጓዛሉ።
ስለመነኩሲቷ መታገት በርካታ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል። ከወራት በፊት ከእግት ያመለጡ ሁለት አውሮፓዊያን በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው ማለታቸው ይታወሳል።
ባለፈው መጋቢት ደግሞ ወንድማቸው በሕይወት እንደሚገኙ የሚያረጋግጥ ደብዳቤ እንደደረሰው ተናግሮ ነበር።
ማሊ ከ2012 ጀምሮ በሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል እየተስፋፋ የመጣውን አክራሪ ኢስላማዊ አስተሳሰብን ለመግታት እየታገለች ትገኛለች።
በተለይ ደግሞ ኢስላማዊ አክራሪ ቡድኖች ሰዎችን በማፈን የገንዘብ ክፍያ በመጠየቅ ይታወቃሉ።
አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንደሚለው ባለፉት አራት ዓመታት ማሊ ውስጥ ከ935 በላይ ሰዎች በታጣቂዎች ታፍነው ተወስደዋል።
ባለፈው ዓመት በማሊ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት የመሩትና የሃገሪቱ ጊዜያዊ መሪ የሆኑት ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ ማሊያዊያንና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ሊያውቁት የሚገባው ታፍነው የተወሰዱት ለማስለቀቅ ጥረት እያደረግን እንዳለ ነው ይላሉ።
ማሊ ውስጥ ያለውን ኢስላማዊ አክራሪነት ለመግታት የፈረንሳይ ወታደሮች ጭምር ተሰማርተው እየተዋጉ ይገኛሉ። ነገር ግን የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ማኽሮን የወታደሮች ቁጥር እንቀንሳለን ብለዋል።
ይህንን ተከትሎ ማሊ ፊቷን ወደ ሩስያ ማዞሯ ተሰምቷል።












