ታንዛኒያዊው ፀሐፊ የዓመቱ የኖቤል የሥነ-ጽሁፍ ዘርፍ አሸናፊ ሆኑ

ታንዛኒያዊው ጸሃፊ አብዱልራዛቅ ጉራህ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ታንዛኒያዊው ጸሃፊ አብዱልራዛቅ ጉራህ

ታንዛኒያዊው ፀሐፊ አብዱልራዛቅ ጉራህ የ2021 የኖቤል የሥነ ጽሁፍ ዘርፍ አሸናፊ ሆኑ።

አብዱልራዛቅ በሥነ-ጽሁፍ ዘርፍ አሸናፊ መሆናቸውን ተከትሎ ከስዊድኑ የኖቤል ሽልማት ድርጅት 10 ሚሊዮን ክራውን [የስዊዲን ገንዘብ] ወይም 1.14 ሚሊዮን ዶላር በሽልማት መልክ ይሰጣቸዋል።

የ73 ዓመቱ አብዱልራዛቅ እስካሁን 10 ልቦለድ መጽሐፍትን ለአንባቢያን ያበቁ ሲሆን 'ፓራዳይዝ' እና 'ዲዘርሽን' የተሰኙት መጽሐፎቻቸው በበርካቶች ዘንድ ተወደውላቸዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1994 ላይ ያሳተሙት 'ፓራዳይዝ' የተሰኘው መጽሐፍ ታንዛኒያ ውስጥ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መወለድና ማደግ ምን እንደሚመስል ቁልጭ አደርገው ያሳዩበት ነው ይባላል።

በዚህ መጽሐፍም ዓለም አቀፉን የ'ቡከር' ሽልማት ለማግኘት ችለዋል።

"ገጸ ባህሪያቱ ሁሌም ቢሆን በባህልና አህጉራት መካከል የተሰነቀሩ፣ በህይወትና በአዲስ ህይወት መካከል የሚመላለሱ ናቸው። በቀላሉ ሊያልፉት የማይችሉት ከባድ እውነታ ውስጥ ናቸው'' ብሏል የኖቤል ኮሚቴ የሥነ-ጽሁፍ ክፍል።

በአውሮፓውያኑ 1948 ዛንዚባር ውስጥ የተወለዱት አብዱልራዛቅ፤ ስደተኛ ሆነው እንግሊዝ የገቡት ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ ውስጥ ነበር።

በቅርቡ በጡረታ እስኪገለሉ ድረስ አብዱልራዛቅ በካንተርበሪ ዩኒቨርሲቲተ ኦፍ ኬንት ውስጥ የእንግሊዝኛ እና ከቅኝ ግዛት በኋላ ስላሉ ሥነ-ጽሁፎች ያስተምሩ ነበር።

አፍሪካውያን ኖቤል ተሸላሚዎች

በአውሮፓውያኑ 1986 ዎሌ ሶይንካ በዘርፉ ካሸነፉ በኋላ አብዱልራዛቅ በሥነ-ጽሁፍ ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚ መሆን የቻሉ ጥቁር አፍሪካዊ ናቸው።

በተለያዩ መስኮች ፍር ቀዳጅ ተግባራትን ያከናወኑ ግለሰቦችን እና ተቋማት በየዓመቱ የሚሸለሙበት የኖቤል ሽልማት በዓለማችን ከሚሰጡ ዕውቅናዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

አልፍሬድ ኖቤል 1888 ላይ በፈረመው ኑዛዜ ያለውን አብዛኛውን ሀብቱን የኖቤል ሽልማት ተብለው ለሚሰጡ ሽልማቶች እንዲውል ተናዟል።

እስካሁንም የኖቤል ሽልማት በሥነ-ጽሁፍ፣ በሳይንስ፣ በሰላም እና በኢኮኖሚክስ ዘርፍ ሲሰጥ ቆይቷል።

ባለፈው ዓመት በዚሁ የሥነ-ጽሁፍ ዘርፍ ማሸነፍ የቻሉት አሜሪካዊው ገጣሚ ሊዊስ ግሉክ ናቸው።

የታንዛኒያዊው ጸሃፊ አብዱልራዛቅ ጉራህ መጽሃፍቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images