ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር አቋርጣ የነበረውን የስልክ ግንኙነት ጀመረች
ሰሜን ኮሪያ ለወራት ያክል አቋርጣ የቆየችውን እና ከደቡብ ኮሪያ መንግሥት ጋር የሚያገናኛትን ነጻ የስልክ መስመር መልሳ ወደ ስራ አስገባች።
ይህም የአገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን፣ ከጎረቤት አገር ደቡብ ኮሪያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሰላምን ለመመለስ ሲባል መልሶ ወደ ስራ ለማስገባት ፈቃደኝነታቸውን መናገራቸውን ተከትሎ የመጣ ነው።
ነገር ግን ፒዮንግያንግ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ የሚደረገው ጥረት በደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት ጸባይ ላይ የተመሰረት እንደሆነ አስታውቃለች።
ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ የጦር ሙከራዎቿን ማጠናከሯ ይታወቃል። ባለፈው ወር ብቻ አራት የሚሳየል ሙከራዎችን ያካሄደች ሲሆን ይህም የጦር መሳሪያ ምርቷን ለመቀነስ እቅድ እንደሌላት ያመላክታል።
የደቡብ ኮሪያ የውህደት ሚኒስቴር ዛሬ ሰኞ ጠዋት እንዳስታወቁት የሁለቱ አገራት አመራሮች ካለፈው ወር ወዲህ የመጀመሪያ የሆነውን የስልክ ልውውጥ አድርገዋል።
"የሁለቱ አገራት የግንኙነት መስመሮች መልሰው ወደ ስራ መግባታቸውን ተከትሎ መንግሥታችን የሁለቱ ኮሪያዎች ግንኙነት መሰረት ጥሏል የሚል እምነት አለን" ሲሉ ሚኒስቴሩ በመግለጫቸው አክለዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት በተደጋጋሚ ሲቋረጥ ብሎም መልሶ ወደ ስራ ሲገባ ቆይቷል።
እኤአ በ 2020 በሁለቱ ኮሪያ መሪዎች መካከል ታቅዶ የነበረው ጉባኤ ሳይካሄድ መቅረቱን ተከትሎ ፒዮንጊያንግ በአገራቱ ድንበር መካከል የሚገኘውን እና የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር የተከፈተውን ጽህፈት ቤት ማፈንዳቷ ይታወሳል።
በተመሳሳይ አመት ሰሜን ኮሪያ ከጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ መሪዎች ጋር የሚያገናኛትን ነጻ የስልክ መስመርን ጨምሮ፣ የነበራትን ሁሉንም ግንኙነት ማቋረጧም አይዘነጋም።
ከአንድ ወር በፊት ነጻ የስልክ መስመሩ ተመልሶ ወደ ስራ ቢገባም በአጭር ግዜ ውስጥ መልሶ ተቋርጦ ነበር።
በሁለቱ ጎረቤት አገራት መካከል የነበረው ጦርነት በ 1953 ቢጠናቀቅም ከዛ ወዲህ የሰላም ስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው እስካሁን ጦርነት ላይ እንዳሉ ይቆጠራል።