"የልጄን አስከሬን በኢንተርኔት ላይ አየሁት" በኢኳዶር ማረሚያ ቤት ልጃቸው የተገደለባቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኢኳዶር የወደብ ከተማ ጉዋያኪል በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ባሉ ተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል በተከሰተ አምባጓሮ ከ100 በላይ እስረኞች ተገድለዋል። አስከሬኖቹን ለመለየት ቀናት እንደሚወስድ የተነገረ ሲሆን ዘመዶችና ቤተሰቦችም በጭንቅት እየጠበቁ ናቸው።
ጋዜጠኛ ብላንካ ሞንዳዳ ፔሳንቴስ መርዶ እየጠበቁ ካሉ ቤተሰቦችን አንዳንዶቹን አነጋግራለች።
በብዙ የጉዋያኪል ሰፈሮች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በነበረበትና በርካታ ሞት በተመዘገባባቸው በመጋቢትና በሚያዝያ ወራት እንኳን እንዲህ የአስከሬን ማስቀመጫዎች በሮች ላይ ዘመድና ቤተሰብ ተሰባስቦ አልታየም።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጊሊርሞ ላሶ የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ሲያሳውቁ፣ በርካታ ቤተሰቦችም የአስረኞቹ አስከሬን ወደተወሰደበት የምርመራ ላቦራቶሪ ሲሯሯጡ ታይተዋል። መርዶን መጠበቅ ቀላል አይደለም። የሚወዷቸው ቤተሰቦች የት እንዳሉ ተርፈውም ከሆነ ዜናውን ለመስማማት በጉጉት እየጠበቁ ይገኛሉ።
እስካሁን ግን መልስ አላገኙም፤ ይባስ ብሎ ፍንዳታ ከጉዋያኪል እስር ቤት መሰማት መቀጠሉና ዓለም አቀፍ የትስስር ሰንሰለት ባላቸው የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ተቀናቃኝ ወንበዴዎች መካከል የተነሳው ፍልሚያ በቁጥጥር ስር ያለመዋሉ ማሳያ ነው።
ባለፈው ሐሙስ አመሻሹ ላይ 900 የፖሊስ መኮንኖችንና ጦሩን ያካተተ ቡድን እስር ቤቱን መቆጣጠሩንና የሟቾች ቁጥርም 118 እንደደረሰ አሳውቋል።
የአስከሬን ምርመራ ከሚደረግበት ስፍራ ውጪ ሲጠባበቁ ከነበሩት መካከል አንዱ የ66 ዓመቱ ጉስታቮ ቪቭስ ሲሆኑ የ24 ዓመቱ ወንድ ልጃቸው በእስር ቤቱ ግርግር ተገድሏል።
"እሱ አሁን እየተነገረ ካለው የሟቾች ዝርዝር ውስጥ የለም፣ ነገር ግን እንደሞተ ተረድቻለሁ፣ ምክንያቱም አስከሬኑን በኢንተርኔት አይቼ ልጄ መሆኑን አውቄያለሁ" ብለዋል።
እንደ ሌሎቹ ሁሉ እሳቸውም በማኅበራዊ ሚዲያ እና በእስረኞች ዘመዶች መካከል ከተጋሩ ምስሎች እና ቪዲዮዎች ነው አሰቃቂውን ዜና የተረዱት።
ሐሙስ እኩለ ቀን ላይ የአስከሬን ምርመራ የሚደረግበት ቦታ በሰዎች ተሞልቷል። የአንዱ እርግማን ለአንዱ ምርቃት እንዲሉ በተጨነቁ ዘመዶች መካከል ገንዘብ ለማግኘት የሚሯሯጡ የቀብር ሠራተኞችም እየተራወጡ ይታያሉ።
በጉዋያኪል ውስጥ በሬሳ ሣጥን እጥረት አንዳንድ ሰዎች የሚወዷቸውን ለመቅበር ካርቶን ለመጠቀም ሲገደዱ ከታዩበት በጣም አስከፊው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቀናት በተቃራኒ በርካታ የሬሳ ሣጥኖችም ተዘጋጅተው ይታያሉ።
የ23 ዓመት ልጇን ዳርዊን ካሚኖን ዕጣፈንታ እንዲነገራቸው ሲጠብቁ የነበሩት ሌላኛዋ ወላጅ ዜናይዳ ሞሪራ እንባዋቸውን በመሃረብ እየጠረጉ ነበር።
የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚ የሆነው ልጃቸው ከሁለት ዓመት በፊት ወንበሮችን ከትምህርት ቤት በመስረቁ ተይዞ ነበር አደገኛ በሚባለው ጉዋያኪል ለእስር የተዳረገው።
"በስርቆት ምክንያት የታሰረ ቢሆንም በገዳዮች፣ በደፋሪዎች እና በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች መካከል ተከቦ ነው የሚገኘው" ይላሉ።
በእስር ቤቱ ውስጥ የደረሰውን እልቂት ቪዲዮዎች ካዩ በኋላ የልጃቸው ዕጣ ፈንታ እንዳስፈራቸው ያስረዳሉ።

"እኔ ካየሁት አስከሬኖች መካከል የልጄ መኖሩን አላውቅም። የተቆረጠ ጭንቅላት አየሁ፣ ፊቱ ከእሱ ጋር ይመሳሰላል፣ ነገር ግን ባለስልጣናቱ ምንም እያሉ አይደለም " ብለዋል በእንባ እየታጥቡ።
ከታሰረ በኋላ በሕገ ወጥ መንገድ በገባ ስልክ ይደውልላቸው ነበር። ነገር ግን ድምፁን ለመጨረሻ ጊዜ ከሰሙ ቀናት ተቆጥረዋል።
ሌላኛዋ ሴት እናቷን ለማረጋጋት እየሞከረች ነው። ረቡዕ ዕለት የፀጥታ ሠራተኞች ማረሚያ ቤቱን እንደበረበሩና ስልኩ ምናልባት ተይዞ ስለሆነ ነው ያልደወለው የሚል ተስፋን እህቱ ሰንቃለች።
ምንም እንኳን ቤተሰቡ ልጃቸው በህይወት አለ የሚል ተስፋ ቢኖራቸውም፣ ምናልባት የከፋ ነገር ተከስቷል በሚል ከአስከሬን ምርመራው ቦታ ውጪ እንደ ሌሎች እየጠበቁ ነበር።
ዘመዶችና ቤተሰቦች ከአስከሬን መመርመሪያ ቤተ ሙከራ አካባቢ ብቻ አይደለም እየጠበቁ የነበሩት። ባለስልጣናቱ የታራሚዎቹን ዕጣ ፈንታ እየተጠባበቁ ያሉ ዘመዶችና ቤተሰቦች ወደ አቤል ጂሜኔስ ስታዲየም እንዲሄዱ ጠይቀዋቸዋል። ዜናዎችንም እንደሚነግሯቸውም ሆነ የሥነ ልቦና ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸውም ቃል ገብተውላቸዋል።
ነገር ግን የ20 ዓመቱን ልጁን እየፈለገ ያለው የ40 ዓመቱ ፔድሮ ሙሪሎ ምንም መረጃ እንዳላገኘ ይናገራል።
"እኔ እንደተባለው ወደ ስታዲየሙ ብመጣም፣ ስሙ ማን እንደሆነና ንቅሳት እንዳለው ከመጠየቅ ውጪ የተነገረኝ ነገር የለም" በማለት የስታዲየሙን ዙሪያ ስለሚጠብቁት ወታደሮች ያስረዳል።
"ለሁለት ቀንና ለሁለት ሌሊት አልተኛሁም። በጣም ስለተረበሸኩኝም ወደ ሥራ መሄድ አልቻልኩም" ይላል።
አብዛኞቹ የሞት አደጋዎች በእስር ቤቱ ከሚገኙት አምስተኛና ስድስተኛ ክንፍ በሚባሉት ክፍሎዎች ውስጥ እንደተከሰተ ይገመታል።
አምስተኛ በሚባለው ክንፍ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ክፍሎች ተቃጥለዋል የሚሉ መረጃዎች አሉ፤ ይህም ቃጠሎው የሞቾችን ማንነት ለመለየት የሚደረገውን ጥረት የበለጠ እንደሚያጓትትና አዳጋች ያደርገዋል።
ከሟቾች በተጨማሪ በርካታ የተጎዱ እስረኞችም ያሉ ሲሆን ማክሰኞ እስከ ረቡዕ ቢያንስ 50 የቆሰሉ እስረኞች ወደ ዴል ጉሶሞ ሆስፒታል መወሰዳቸውን አንድ ዶክተር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ ውስጥ ከአስር ቤቱ የመጡ በርካታ ታራሚዎች መሰባሰባቸውን ተከትሎ በተቀናቃኞቹ የወሮበላ ቡድኖች አባላት መካከል ሌላ ፍልሚያ ሊነሳ ይችላል የሚል ፍራቻ እንዳለ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ፖሊስ የማረሚያ ቤቱን እያንዳንዱን ክፍል ሲፈትሽ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚልም ሥጋት አለ።












