የአሜሪካን የማዕቀብ ትዕዛዝ ተከትሎ ህወሓት እና የአማራ ክልል ምን አሉ?

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አርብ ዕለት በሠሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ውስጥ ጥሰቶችን ፈጽመዋል የተባሉ አካላት ላይ ያነጣጠረ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መፈረማቸው ይታወሳል።

ማዕቀቡ በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት፣ የአማራ ክልል አስተዳደርና የህወሓት አባላትን ተጠያቂ የሚያደርግ ነው።

ይህ የማዕቀብ ትዕዛዝ ግጭቱ እንዲራዘም አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ያደናቀፉ፣ ተኩስ እና ጦርነቱ እንዳይቆም ያደረጉ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሏል።

በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ግጭቱን ለማስቆም አስቸኳይ እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ አሜሪካ ልትጥል ያሰበችውን ማዕቀብ ለማዘግየት ዝግጁ መሆኗንም በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል ጨምራ አስታውቃለች።

የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ይህን የማዕቀብ ትዕዛዝ የፈረሙት በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ግጭቱን በንግግር ለመፍታት በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲነጋገሩ ለማስገደድ ነው።

ይሁን እንጂ፤ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን ትዕዛዝ ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያን የተመለከተው የአሜሪካ ፖሊሲ ከሰብዓዊ መቆርቆር ያለፈ ነው ሲሉት፤ የአማራ ክልል መንግሥት በማዕቀብ ትዕዛዙ ውስጥ ክልሉ መካተቱ አሳስቦኛል ብሏል። ህወሓት በበኩሉ የፕሬዝደንቱ ውሳኔ አግባብ ነው ብሏል።

ጠቅላይ ሚንትር ዐ

የፕሬዝደንት ጆ ባይደን ውሳኔ ከተሰማ በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ለፕሬዝደንቱ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ላይ አሜሪካ ከኢትዮጵያ አንጻር የምትከተለው ፖሊሲ ያልተጠበቀ ከመሆኑ ባሻገር ከሰብዓዊ መቆርቆር ያለፈ ነው ሲሉ ተችተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግልጽ ደብዳቤያቸው ህወሓት በአፋርና በአማራ በንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሰውን ጉዳት በማስታወስ መላው ዓለም በተሳሳተ ምክንያት አይኑን በኢትዮጵያ ላይ ማተኮሩን በመጥፎ በማንሳት ህወሓትን በይፋ ተጠያቂ ለማድረግ አልቻለም ሲሉ ወቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የአሜሪካ አስተዳደሮች በጥድፊያ በተወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት ከመፍትሄ ይልቅ በርካታ ሕዝቦችን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲወድቁ ማድረጉን በመግለጽ፤ "ኢትዮጵያ ከሚሊዮኖች ደኅንነት ይልቅ ሥልጣንን በሚያስቀድሙ ግለሰቦች ለተቀናበረ ግፊት አትንበረከክም" ብለዋል።

ህወሓት

ህወሓት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ ፕሬዝደንት ባይደን እና አስተዳደራቸው በኢትዮጵያ ለተከሰተው ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ ለመስጠት የሚያደርገው ተከታታይ እና ገንቢ ጥረት የሚበረታታ ነው ብሏል።

ህወሓት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ የአሜሪካ መንግሥት ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ድርድሩን የማስተባበር ኃላፊነት እንዲወስድ ጠይቋል።

በትግራይ ለተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ መንግሥታትን እንዲሁም የአማራ ክልልን ተጠያቂ ያደረገው ህወሓት፤ በትግራይ የተደቀነው የረሃብ ስጋት ሚሊዮኖችን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብሏል።

ህወሓት በግጭቱ በትግራይ ተወላጆችም ሆነ በሌሎች ላይ ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ የሆኑትን ለመለየት በሚደረገው ምርመራ የትግራይ መንግሥት ተባባሪ ይሆናል ብሏል።

አማራ ክልል

የአማራ ክልል መንግሥት በበኩሉ ክልሉ የዕቀባ ትዕዛዝ ውስጥ መካተቱ አሳሳቢ ነው ብሏል።

የክልሉ መንግሥት "የአማራ ሕዝብ ወደ መኖሪያው ከመጡ ወራሪዎች እና ወንጀለኞች እራሱን እየተከላከለ ነው" ስለማለቱ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ክልሉ ጨምሮም የአሜሪካ መንግሥት እና ግምጃ ቤቱ በሚያደርጉት ምርመራው እንደሚተባበር አስታውቋል።

ኤርትራ

የኢትዮጵያን መንግሥት በመደገፍ በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፏል የሚባለውና ሠራዊቱ በበርካታ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚከሰሰው የኤርትራ መንግሥት ግን አስካሁን በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ውሳኔ ላይ ያለው ነገር የለም።

አሜሪካ ቀደም ሲል በጦርነቱ ውስጥ ጉልህ ሚና አላቸው በተባለ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በኤርትራ መንግሥት፣ በአማራ ክልል አስተዳደርና በህወሓት አመራሮች ላይ የጉዞ ዕቀባ መጣሏን አስታውቃ ነበር።

ባለፈው ነሐሴ ወር ደግሞ የኤርትራ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በሆኑት በጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ ላይ የንበረት እገዳ መጣሏን አስታውቃ ነበር። ይህንንም እርምጃ የኤርትራ መንግሥት ተቃውሞት ነበር።

አሁን በርካታ እገዳዎች የተካተቱበትና ኤርትራንም የሚመለከተውን የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትዕዛዝን በተመለከተ ከአሥመራ በኩል በይፋ የተባለ ነገር የለም።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ግጭት ከተከሰተ ድፍን አንድ ዓመት ሊሞላው በጣት የሚቆጠሩ ወራቶች ብቻ ይቀሩታል።

ባለፉት ወራት በተካሄደው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ጦርነቱን ተከትሎ በተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስም በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጧል።

ከወራት በፊት የፌደራሉ መንግሥት መቀለን ጨምሮ ከትግራይ አካባቢዎች መውጣት መጀመሩን ተከትሎ የህወሓት አማጺያን በመልሶ ማጥቃት ወደ አፋር እና አማራ ክልል ዘልቀው መግባታቸው ይታወሳል።

የፌደራሉ መንግሥት ከሌሎች ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በመሆን ከህወሓት ጋር የሚያደረገው ጦርነት እንደቀጠለ ነው።