አዲሱ የጆሃንስበርግ ከተማ ከንቲባ በመኪና አደጋ ሕይወታቸው አለፈ

የፎቶው ባለመብት, SOUTH AFRICA'S PRESIDENCY
የ46 ዓመቱ የጆሃንስበርግ ከተማ ከንቲባ ጆሊዴ ማቶንጎ ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ ሕይወታቸው አለፈ።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በከንቲባው ህልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።
ከንቲባው ሕይወታቸው ከማለፉ በፊት ከፕሬዘዳንቱ ጋር የምርጫ ቅስቀሳዎችን ሲያካሂዱ ነበር። የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከንቲባው አንድ እግረኛን ለማዳን ባደረጉት ጥረት ነበር ከሌላ ተሸከርካሪ ጋር ተጋጭተው ሕይወታቸው ያለፈው።
ቢሆንም ግን እግረኛው ግለሰብም ሆነ የሌላኛው ተሽከርካሪ ሾፌር በተመሳሳይ በአደጋው ምክያት ሕይወታቸው አልፏል።
በተጨማሪም የከንቲባው ሁለት ጠባቂዎች በአደጋው ሳቢያ በደረሰባቸው ጉዳት በሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው።
ማቶንጎ ወደ ስልጣን የመጡት ከአንድ ወር በፊት ሲሆን በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈውን የቀድሞውን ከንቲባ ተክተው ነበር ሹመቱን ያገኙት።
የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከንቲባው ከዚምባብዌ የመጣ ስደተኛ ቤተሰብ ልጅ የነበሩ ሲሆን ገና ከ13 ዓመታቸው ጀምሮ በደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድ ትግል ውስጥ ተሳታፊ ነበሩ።
በተጨማሪም የደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ የሆነው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) አባልም ነበሩ።
በመጪው ኅዳር 1 ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የአካባቢ ምርጫ የደቡብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ዋና ከተማ በሆነችው ጆሃንስበርግ ውስጥ ለማሸነፍ ፓርቲያቸው ለሚያደርገው ዘመቻ ግንባር ቀደም ተወዳዳሪ ይሆናሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
"ከንቲባ ማቶንጎ ከእኔ እና ከሶዌቶ ነዋሪዎች ጋር ውለው ብዙም ሳይቆይ ይህንን አሳዛኝ ሁኔታ ስሰማ ለማመን የሚከብድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ለዚህ ድንገተኛ አደጋ አእምሯችንን ቀድሞ ሊያዘጋጀው የሚችል ምንም ነገር አልነበረም። የአገራችን የኢኮኖሚ ማዕከል ሁለተኛ ከንቲባዋን በሁለት ወር ውስጥ አጥታለች" ሲሉ ፕሬዘዳንት ራማ ፎሳ ተናግረዋል።
የጋውቴንግ ግዛት መሪ ዴቪድ ማኩራ በከንቲባው ሞት ልባቸው መሰበሩን ተናግረዋል።
ማቶንጎ የጆሃንስበርግ ከንቲባ ሆነው ከመመረጣቸው በፊት ለበርካታ ዓመታት የምክር ቤት አባል ሆነው አገልግለዋል።












