ፈረንሳይ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር የነበራትን የመከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ በድንገት ሰረዘች

በህር ስርጓጅ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Defence

የፈረንሳይ የመከላከያ ሚኒስትር ከዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ጋር በመከላከያ ዙርያ የነበራቸውን ስብሰባ በድንገት ሰረዙ።

ፈረንሳይ ከዚህ ውሳኔ የደረሰችው የቢሊዮን ዶላር የኑክሌየር ባሕር ሰርጓጅ መርከብ ሽያጭ-ግዢ ስምምነትን አጋሮቼ በምትላቸው በአሜሪካና ዩኬ መቀማቷን ተከትሎ ነው።

አውስትራሊያ ከፈረንሳይ ጋር አድርጋው የነበረውንና ዓመታትን ያስቆጠረ የባሕር ሰርጓጅ ቴክኖሎጂ ስምምነትን ሰርዛ ከአሜሪካና ዩኬ ጋር አዲስ ስምምነት መፈጸሟ ፈረንሳይን ክፉኛ አስቆጥቶ እንደነበር ይታወሳል።

ፈረንሳይ በወዳጅ አገር መከዳት ያማል ያለች ሲሆን 'ከጀርባ በስለት የመወጋት ያህል ነው' ስትል 'ክህደቱ' ያደረሰባትን ጉዳት ስትገልጽ ነበር፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን ፈረንሳይ አምባሳደሯን ለምክክር ከአሜሪካ እስከመጥራት ደርሳለች።

እንዲህ ዓይነቱ ነገር ጥብቅ ወዳጅ አገራት እንደሆኑ በሚነገርላቸው ምዕራባዊያን መካከል እምብዛምም የሚያጋጥም ክስተት አይደለም።

ወትሮም እየሻከረ የነበረውን የዩኬና የፈረንሳይን ግንኙነት ይህ አውከስ በሚል ምህጻር የሚጠራው ስምምነት አበላሽቶት ፈረንሳይ ከዩኬ ጋር የነበራትን የመከላከያ ስምምነት እንድትሰርዝ አደርጓታል፡፡

በዚህ የመከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ የፈረንሳይ የመከላከያ ሚኒስትሯ ከዩኬ አቻቸው ጋር በሎንዶን ተገኝተው የሚመክሩበት ጉባኤ ነበር።

የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ፈረንሳይ በባሕር ሰርጓጅ ቴክኖሎጂ ስምምነት እምብዛምም መጨነቅ አይኖባትም ሲሉ ተደምጠዋል።

ፈረንሳይ ለአውስትራሊያ በኒክሊየር የሚታገዝ የባሕር ሰርጓጅ መርከቦች ቴክኖሎጂን ለማቅረብ ስምምነት ፈጽማ የነበረው እአአ በ2016 ነበር። ይህም 12 ባሕር ሰርጓጅ መርከቦችን መገንባትን ይጨምራል።

የዚህ ስምምነት የገንዘብ መጠንም 37 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል።

ሆኖም አውስትራሊያ ጉዳዩን ለፈረንሳይ ሳታሳውቅ ስምምነቷን አፍርሳ ከአሜሪካ ጋር አዲስ ስምምነት ውስጥ መግባቷ የተሰማው ባለፈው ሳምንት ነበር።

የዚህ ስምምነት ዋንኛ ዓላማውም በአካባቢው ጡንቻዋ እየፈረጠመ የመጣውን ቻይናን በጋራ መቋቋም ነው።

ይህ ስምምነት አውስትራሊያ የኑክሊየር ባሕር ሰርጓጅ መርከብ ባለቤት ለመሆን በዓለም 7ኛዋ አገር እንድትሆን ያስችላታል።

እስከዛሬ በዚህ ቴክኖሎጂ ባለቤት የሆኑት አሜሪካ፣ ዩኬ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ህንድና ሩሲያ ብቻ ነበሩ።

ቻይና በበኩሏ ይህን የሦስትዮሽ ስምምነት ክፉኛ የተቸችው ሲሆን አውካስ ስምምነትን ያደረጉትን ሦስቱን አገራት ማለትም አውስትራሊያ፣ አሜሪካንና ዩኬን 'የቀዝቃዘው ጦርነት አስተሳሰብ የተጸናወታቸው' ስትል ወርፋቸዋለች።