በኬንያ በተከሰተ ድርቅ ሕጻናት መራር ቅጠሎችን ለመብላት ተገደዋል ተባለ

በምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኬንያ በተከሰተ ድርቅ ምክንያት ወላጆች ልጆቻቸውን ለምግብነት የማይውሉ መራር ቅጠሎችን ለመመገብ ተገደዋል ተባለ።

በኬንያ ኪፊሊ በተባለ ግዛት በተከሰተ ድርቅ ምክንያት ከ20 በላይ ሰዎች ሆስፒታል የገቡ ሲሆን የአንድ ሰው ሕይወት ስለማለፉ ተዘግቧል።

ወደ 250ሺህ የሚጠጋ ሕዝብ ደግሞ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል ሲሉ የግዛቷ አስተዳዳሪዎች ይፋ አድርገዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የግጦሽ ሳር ባለመኖሩ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ከብት ስለሞመታቸውም ተዘግቧል።

የ8 ልጆች እናት የሆነችው ካሁዳ ኮምቤ ለቢቢሲ እንደተናገረችው፤ ድርቅ መቋቋም የሚችል የዛፍ ቅጠል ልጆቿን እየመገበች እንደሆነ ትናገራለች።

"በጣም መራር ነው (የዛፉ ቅጠል)፤ ምንም አማራጭ ስለሌለን እንበላዋለን። ለቀናት ምንም ነገር ሳንመገብ ልንቆይ እንችላለን። ሰውነታችን ምግብ የበላን እንዲመስለው ለማታለል ይሄን ነው የምንበላው" በማለት የ8 ልጆች እናቷ ታስረዳለች።

የነበሯት የቤት እንስሳት በሙሉ አልቀው አንድ ላም ብቻ እንደቀራትም ትናገራለች።

ካሁዳ ኮምቤ አልፎ አልፎ በእርዳታ በሚያገኙት የበቆሎ ዱቄት በኬንያውያን ዘንድ በስፋት የተለመደውን ኡጋሊ የተሰኘውን ምግብ ለልጆቿ እንደምትሰራ ተናግራለች።

የኬንያ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ባለፈው ሳምንት ድርቅ ብሔራዊ አደጋ ነው ሲሉ አውጀው ነበር። ፕሬዝደንቱ የግምጃ ቤት ኃላፊው እና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስቴር በድርቁ ምክንያት የተጎዱ የቤተሰብ አባላትን እንዲረዱ መመሪያ ሰጥተዋል።

ኬንያ ካላት 47 ግዛቶች በ13ቱ ድርቅ ተከስቷል። በዚህም ከ2 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለጉዳት ተጋልጧል።