የአፍጋኒስታን ቀውስ፡ የአሜሪካው ጀነራል 'ጨካኙ ታሊባን' ይለወጥ እንደሆነ ግልፅ አይደለም' አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ታሊባንን "ጨካኙ ቡድን' ሲሉ የገለፁት የአሜሪካ ከፍተኛ ጀነራል ታሊባን ይለወጥ እንደሆነ ግልፅ አይደለም አሉ።
ጀነራል ማርክ ሚሌይ አሜሪካ ወደፊት ከእስላማዊ ታጣቂዎች ጋር በመተባበር ፀረ ሽብር ተግባራትን ማስተባበር ትችላለች ብለዋል።
የአሜሪካ ጦር ማክሰኞ ዕለት ከአፍጋኒስታን የወጣ ሲሆን፤ አሜሪካ ታሊባንን ለማስወጣት ወረራ ከጀመረች ከ20 ዓመታት በኋላ በአፍጋኒስታን የነበራት ጦርነት አብቅቷል።
አገሪቷን የተቆጣጠሩት እስላማዊ ታጣቂዎቹ አዲስ መንግሥት እንደሚመሰርቱ ይጠበቃል።
ጀነራል ሚሌይ ከአሜሪካው መከላከያ ዋና ኃላፊ ልሎይድ ኦስቲን ጋር ንግግር ያደረጉ ሲሆን፤ የመጨረሻው የአሜሪካ ጦር አፍጋኒስታንን ለቆ ከወጣ በኋላ ያደረጉት የመጀመሪያው ሕዝባዊ ንግግራቸው ነው።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ጦሩ በወጣበት አግባብ በሰፊው ትችት ቀርቦባቸዋል።
የአሜሪካ ጦር መውጣቱ አሜሪካ ለዓመታት ያሰለጠነቻቸውና በገንዘብ የደገፈችው የአፍጋኒስታን የፀጥታ ኃይል ባልተጠበቀ መልኩ እንዲፈርስ አድርጎታል።
የታሊባን መብረቃዊ ግስጋሴ ለአሜሪካ ሲሰሩ የነበሩትን በሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ዜጎችን እና የአካባቢውን ነዋሪዎች የማስወጣቱን ጥረት ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል።
ረቡዕ ዕለት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ጀነራል ሚሌይ እና ዋና ኃላፊው ኦስቲን አፍጋኒስታንን ሲያገለግሉ የነበሩትንና ከአፍጋኒስታን የማስወጣቱን ተልዕኮ የተወጡ ወታደሮችን አመስግነዋል።
ከአውሮፕላን ማረፊያው ለመውጣት ከታሊባን ጋር ስለነበራቸው ትብብር የተጠየቁት ኦስቲን "በጣም ውስን በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከታሊባን ጋር ስንሰራ ነበር። የነበረው ያ ነው። የምንችለውን ያህል ሰዎች ለማስወጣት ችለናል" ብለዋል።
"በጦርነት ወቅት በማስወጣት ተልዕኮው እና በኃይላችን ላይ የሚያጋጥመውን አደጋ ለመቀነስ ማድረግ የምንፈልገውን ሳይሆን ማድረግ ያለብን ነው የምናደርገው" ሲሉ ጀነራል ሚሌይ ተናግረዋል።
ጀነራሉ አክለውም አሜሪካ ወደፊት ከእስላማዊ ታጣቂ ጋር ግንኙነት ባላቸው አይኤስ-ኬ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ከታሊባን ጋር በትብብር ልትሰራ ትችላለች ብለዋል።
አይኤስ ኬ ቡድን ባለፈው ሳምንት በካቡል አየር ማረፊያ በተፈፀመውና 13 የአሜሪካ ወታደሮችን ጨምሮ 170 ሰዎችን የገደለው ጥቃት ተጠያቂ ተደርጓል።
አይኤስ ኬ በአፍጋኒስታን ካሉ ጂሃዳዊ ቡድኖች በጣም አክራሪውና አጥፊው ቡድን ነው።
ቡድኑ ከታሊባንም ጋር መሠረታዊ ልዩነት ያላቸው ሲሆን ጂሃዳዊ ድርጊቱንና ውጊያ በመተዋቸው ታሊባኖችን ይወቅሷቸዋል። ኦስቲን በበኩላቸው ከታሊባን ጋር ወደፊት ስለሚኖራቸው ትብብር ምንም አይነት ትንበያ ማስቀመጥ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ ባለሥልጣናት "እኛ በአይኤስ ኬ ላይ ማተኮራችንን፣ ግንኙነታቸውን መገንዘባችንን እና ወደፊት ስለሚኖረን ግንኙነት ስንመርጥ፤ ስለሰሩት ሥራ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ማንኛውንም ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ" ብለዋል።
ከአፍጋኒስታን በማስወጣቱ ተልዕኮ በአጠቃላይ ከ123 ሺህ በላይ ሰዎች ከታሊባን ለመሸሽ ሲጥሩ ታይተዋል።
አሜሪካ ከ100 እስከ 200 የሚሆኑ አሜሪካውያን እስካሁን በአፍጋኒስታን እንደሚገኙ ገልጻለች።
በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የፖለቲካ ጉዳዮች ባለሥልጣን ቪክቶሪያ ኑላንድ "የቀሩ የአሜሪካ ዜጎችንና ለአሜሪካ ሲሰሩ የነበሩ ሰዎችን ለማስወጣት ሁሉንም አማራጮች እየተመለከትን ነው" ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ በበኩላቸው ምን ያህል የዩናይትድ ኪንግደም ሰራተኞች በአፍጋኒስታን እንደቀሩ እርግጠኛ እንዳልሆኑ፤ ነገር ግን በዝቅተኛ መቶዎች የሚቆጠሩ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ታሊባኖች የመጨረሻውን የውጭ ኃይሎች መውጣትን እያከበሩ ሲሆን መንግሥት መመስረት ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል።
በኳታር የሚገኘው የታሊባን የፖለቲካ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ ሸር አባስ ስታኔክዛ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት አዲስ መንግሥት ይመሰረታል። ምክትል ኃላፊው በዝቅተኛ የሥራ ኃለፊነት ላይ ለሴቶችም ቦታ እንደሚኖር ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ላለፉት አስርት ዓመታት መንግሥትን ያገለገሉ በዚህ አይካተቱም ብለዋል ምክትል ኃላፊው።












