አፍጋኒስታን፡ የአሜሪካ ጦር በአፍጋኒስታን ምን ጥሎ ወጣ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካቡል በሚገኘው ሃሚድ ካርዛይ አየር ማረፊያ ውስጥ የታሊባን ወታደሮች የአሜሪካ ጦር ጥሎ የወጣቸውን የጦር አውሮፕላኖች እና የጦር መሳሪያዎች ይዘው የሚያሳዩ ምስሎች እየወጡ ነው።
በቀነ ገደቡ መሠረት የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን ሲወጣ በጠቅላላው 73 አውሮፕላኖች፣ 100 ተሽከርካሪዎች እና ሌሎች ቁሳቁሶች ጥሎ ወጥቷል።
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ እዝ ኃላፊ ጀነራል ኬኔዝ ማኬንዚ ጦሩ ጥሎ የወጣው ንብረት በሙሉ ዳግም ጥቅም ላይ እንዳይውል ተደርጓል ይላሉ።
"አውሮፕላኖቹም በፍጹም ዳግም አይበሩም" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ጦር በካቡል ጥሎ ከወጣቸው አውሮፕላኖች መካከል ጥቃት ለመሰንዘር እና ለስለላ የሚውል ኤምዲ-530 ሄሊኮፕተሮች እና ኤ-29 አነስተኛ አውሮፕላኖች ይገኙበታል።
ሰኔ ወር ላይ የአፍጋኒስታን ጦር በአሜሪካ መንግሥት የቀረቡ 43 ኤምዲ-530 ሄሊኮፕተሮች እና 23 ኤ-29 አነስኛ አውሮፕላኖች ነበሩት።
የአንድ ኤ-29 አውሮፕላን ዋጋ 10 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል።
የአሜሪካ ጦር ሠራዊት የደንብ ልብስ እና ትጥቅ የታጠቁ የታሊባን ታጣቂዎች የአሜሪካ ጦር ጥሎት የሄደውን ግዙፉ ሲኤች-46 ሄሊኮፕተር ሲቆጣጠሩ የሚያሳይ ምሥል የኤልኤ ታይምስ ዘጋቢ በትዊተር ገጹ አጋርቷል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
የአሜሪካ መንግሥት በካቡል በሚገኘው ኤምባሲው የነበሩ ሰራተኞቹን ለማስወጣት ጥቅም ላይ አውሎት የነበረው ሄሊኮፕተር ሲኤች-46 ዳግም ጥቅም ላይ እንዳይውል በማድረግ ጥሎት ወጥቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ እዝ ኃላፊ ጀነራል ማኬንዚ ጦሩ ወደ 70 የሚጠጉ የፈንጂ ፈንዳታን መቋቋም የሚችሉ ተሽከርካሪዎችን ዳግም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አድርጎ መውጣቱን ተናግረዋል።
ይህ አይነት ተሽከርካሪ የአንዱ ዋጋ ከ500 ሺህ-1 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል።
የአሜሪካ ጦር ቢያንስ አንድ ሲ-130 ሄርኩሌስ ማጓጓዣ አውሮፕላን በአየር ማረፊያው ጥሎ ወጥቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በተቀረው የአገሪቱ ክፍል ግን የአፍጋኒስታን መንግሥት ጦር የታሊባን ጦርን ሲሸሹ ከአሜሪካ ያገኙት ጦር ቁሳቁሶች ሳያወድሙ ነው።
እስካሁን ትክክለኛውን ቁጥር ማወቅ ባይቻልም በአፍጋኒስታን ጦር ቁጥጥር ይዟቸው ከነበሩት መካከል፤ 33 ዩኤች-60 ብላክ ሆውክ ሄሊኮፕተሮችን ጨምሮ 167 አውሮፕላኖች በታሊባን እጅ እንደሚገኙ ይታመናል።
ባለሙያዎች ታሊባን የአሜሪካ ጦር ጥሎ የወጣቸውን ቁሳቁሶች በአነስተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ ሊያውላቸው ይችላል ይላሉ።
ነገር ግን የታሊባን አብራሪዎች ስልጠና አለመውሰዳቸው እና የመለዋወጫ አቅርቦት አለመኖር ታሊባን የአሜሪካንን ጦር አውሮፕላኖች እንዳይጠቀም እክል እንደሚሆኑበት ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
ከዚህ ውጪ የታሊባን ወታደሮች ሌሎች የአሜሪካ ጦር መሳሪያዎችን እየተጠቀሙ ነው።
የታሊባን ልዩ ኃይል አባላት አሜሪካ ሰራሹን ኤም4 ጦር መሳሪያ ታጥቀው ታይተዋል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ሌላው ለታሊባን ወታደሮች ከፍተኛ ጥቅምን ይሰጣሉ የተባሉት የጨለማ መነጽሮች ናቸው። አሜሪካ ባለፉት 20 ዓመታት በአፍጋኒስታን በቆየችባቸው ዓመታት 16 ሺህ ገደማ መነጽሮችን ለመንግሥት ጦር አበርክታለች።












