በጦርነቱ ከአፋር ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ከ112 ሺህ በላይ መድረሱ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, WFP Ethiopia
በአፋር ክልል ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ112 ሺህ በላይ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ አስታውቋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ከአፋር ክልል እና ከፌደራል መንግሥት ጋር በመሆን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እያደረስኩ ነው ብሏል።
እስካሁን ድረስ ባለው 30 ሺህ ለሚሆኑና በአምስት ወረዳዎች ላሉ ቤተሰቦች ስንዴ፣ የጥራጥሬና የአትክልት ዘይት ማድረስ መቻሉንም የማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስፍሯል።
በትግራይ ኃይሎችና በፌደራሉ መንግሥት መካከል የተነሳው ጦርነት አስረኛ ወሩን ያስቆጠረ ሲሆን ወደ አጎራባች ክልሎችም ተዛምቶ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን አፈናቅሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባደረጉት ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ተዋጊዎች ተገድለዋል።
ከወራት በፊት የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ወታደሮቹን ከመዲናዋ መቀለ እንዳስወጣ ቢገልፅም ህወሓት በበኩሉ መቀለን በኃይል እንደተቆጣጠረ ተናግሯል።
የፌደራሉ መንግሥት የተኩስ አቁም በማወጅ ከትግራይ ለቆ ከወጣበት ምክንያቶች መካከል አብዛኛዎቹ የህወሓት የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች በመገደላቸውና በመታሰራቸው እንዲሁም የቀሩትን ጥቂት የህወሓት አመራሮች ለመያዝ ሲባል ጦርነቱን መቀጠል አስፈላጊ ባለመሆኑ ነው ተብሏል።
በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች የግብርና ወቅታቸውን እንዳይስተጓጎል፣ የረድዔት ድርጅቶች የበርካቶችን ህይወት እንዲያድኑ እድል ለመስጠት ነው የሚል መሆኑንም አስታውቋል።
ህወሓት በስምምነት ላይ የተደረሰ የተኩስ አቁም እንደሚቀበል ያስታወቀ ሲሆን ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ከክልሉ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቀው ይገኝበታል።
ባለፉት ወራት ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲመረመሩ እንዲሁም ቴሌኮም፣ መብራትና የአውሮፕላን በረራን ጨምሮ የተቋረጡ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲጀመሩም ጠይቋል።
በአሁኑ ወቅት የጦርነት ክተት ጥሪ በየቦታው በሚቀርብበት በዚህ ወቅት ግጭቱ ወደ አዲስ እና ይበልጥ ደም አፋሳሽ ወደ ሆነ ምዕራፍ ሊያመራ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።












