ዩኤስኤይድ የምግብ እርዳታ ለወታደሮች አድርጓል መባሉን እንደማይቀበል አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) የምግብ እርዳታ ለትግራይ ወታደሮች ሆን ብሎ ወይም በፈቃደኝነት ይሰጣል የሚለውን ማንኛውንም ክስ እንደማይቀበለው አስታውቋል።
በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ ድርጅቱ የሚያደርገውን የምግብ ስርጭት እንደሚከታተልና ድጋፉም ችግረኛ ለሆኑ ነዋሪዎች እንጂ ለተዋጊዎች አይደለም ብሏል።
ከሰሞኑ ትግራይ ውስጥ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ለህፃናትና እናቶች የሚመጡ ሃይል ሰጪ ምግቦችን ለህወሃት እየሰጡ ነው በሚል በሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተነግሯል።
ከነዚህም መካከል ከሰሞኑ ተማረከ በተባለ የህወሃት አባል ዩኤስኤይድ የሰጠው ሃይል ሰጪ ብስኩት በእጁ ይዞ ተገኝቷል በሚል ተዘግቧል።
ዘገባዎቹ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንን ዋቢ በማድረግ የእርዳታ ተቋማቱ ከቆሙለት ዓላማ በተቃራኒው ቡድኑን እየደገፉ ነው የሚል ክስ አቅርበዋል።
ዩኤስኤይድ ለተዋጊዎች እርዳታ እየሰጠ ነው የሚለውን ክስ ባይቀበለውም ሆኖም በአብዛኛውን ጊዜ በግጭት አካባቢዎች ታጣቂዎች እርዳታ ከሚፈልጉ ሰዎች እንደሚሰርቁ አስፍሯል።
ዩኤስኤይድ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ህይወት አድን ምግብ እና እንክብካቤ ትልቁ ለጋሽ መሆኑን አስታውሶ በአሁኑ ጊዜ በመላው አገሪቱ ውስጥ ካለው ህዝብ 7 በመቶ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ዜጎች እየመገበ መሆኑንም ገልጿል።
በተያያዘ ዜና ከሰሞኑ የድርጅቱ ኃላፊ ሰማንታ ፓወር በትግራይ ክልል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በነበሩት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የእርዳታ ድርጅቶች ለተረጂዎች የሚያቀርቡት ምግብ ሊያልቅባቸው እንደሆነ አሳውቀዋል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ አደጋ በተጋለጡበት በትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ የየኤስኤይድ እና ሌሎች ድርጅቶች የእርዳታ ምግብ ማከማቻ መጋዘኖች ባዶ ናቸው በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ይህ የእርዳታ ምግብ እጥረት የተከሰተው ምግብ ባለመኖሩ ምክንያት ሳይሆን "የአየርና የመንገድ እርዳታ አቅርቦት መስመሮችን ጨምሮ የእርዳታ አቅርቦትና የእርዳታ ሠራተኞችን ሥራ የኢትዮጵያ መንግሥት በማደናቀፉ ነው" ሲል መግለጫው ከሷል።
ስለዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ የእርዳታ አቅርቦት በፍጥነት ወደ ትግራይ ክልል እንዲቀርብ የኢትዮጵያ መንግሥት በአስቸኳይ እንዲፈቅድ ጠይቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በባለፈው ሳምንት አርብ በሰጠው መግለጫ መንግሥት ሆን ብሎ እርዳታ እንዳይደርስ እያገደ ነው የሚለውን ውንጀላ ውድቅ አድርጎታል።












