ከትግራይ ዩኒቨርስቲዎች ከ10ሺህ በላይ ተማሪዎች መመለሳቸውንና ለወደፊቱም አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ተገለፀ

መቀለ ዩኒቨርስቲ

የፎቶው ባለመብት, Mekelle University facebook page

በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ይማሩ የነበሩ 10 ሺህ 164 ተማሪዎችን እስከ ኮምቦልቻና አዲስ አበባ ድረስ ማጓጓዝ መቻሉን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር)ን በፃፉት ደብዳቤና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በማህበራዊ ትስስር ገፅ በሰፈረው መሰረት ተማሪዎቹ ከአዲግራት፣ አክሱም፣ የመቀሌና የራያ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ናቸው።

ከሐምሌ ጀምሮ የክረምት ወራት የዕረፍት ጊዜ ቢሆንም በትግራይ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ ወደየመጡበት አካባቢያቸው ለመጓዝ ተቸግረው መቆያታቸው ይታወሳል።

እስከ ነሐሴ 6፣ 2013 ዓ.ም ባለው ወቅት በባለፉት ሶስት ሳምንታትም ከአዲግራት 2 ሺህ 355፣ ከአክሱም 2 ሺህ 992፣ ከመቀለ 3 ሺህ 668፣ ከራያ 1 ሺህ 149 ተማሪዎችን በአጠቃላይ 10 ሺህ 164 ተማሪዎችን በሰመራ ዩኒቨርስቲ በኩል ማጓጓዝ እንደተቻለም ተገልጿል።

ከጦርነቱም ጋር ተያይዞ ተማሪዎቹ በከፍተኛ ፈተና ውስጥ እንደነበሩ የተጠቆመ ሲሆን የዕረፍት ወቅታቸውም ለአንድ ወር ያህል የባከነ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ የእረፍት ጊዜ እንደሚሰጣቸውም መግለጫው አስፍሯል።

ከዚህም በተጨማሪም በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከአዲግራት፣ አክሱምና መቀለ ዩኒቨርስቲዎች ሊመረቁ የነበሩና ያልተጠናቀቀ የትምህርት ፕሮግራም ያላቸውንም በተመለከተ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥም ተጠቁሟል።

ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁበትና የሚመረቁበትንም ሁኔታ እንደሚያመቻችም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በሌላ በኩል ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በትግራይ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች የክረምት ፕሮግራም የሚከታተሉ ተማሪዎች ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ወደተቋማቱ መጓዝ አለመቻላቸውም ተገልጿል።

ለነዚህም ተማሪዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት ትምህርት ለመከታተል ዕድል እንደሚኖርና በትዕግስት እንዲጠባበቁ መልዕክቱን አስተላልፏል።