የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሣሪያ ወደ ትግራይ አጓጉዟል መባሉን አስተባበለ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ምስል

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Airlines

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሣሪያዎችን እና ወታደሮችን ወደ ትግራይ ክልል በማጓጓዝ ላይ ይገኛል በሚል በማህበራዊ ድር አምባዎች እየተሰራጩ ያሉትን መረጃዎች “መሠረተ ቢስ” ሲል በጥብቅ አስተባበለ።

አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ "ከሕዳር 2013 ጀምሮ ወደ ትግራይ ክልል የሚገቡ እና የሚመጡ በረራዎች በሙሉ መቋረጣቸው ይታወሳል” ብሏል።

የአየር ክልል ተመልሶ በተከፈተበት ወቅትም ዜጎችን ወደ ክልሉ በማመላለስ የበረራ አገልግሎት ይሰጥ አንደነበር አስታውሷል።

“የአየር ክልሉ እንደገና ከተዘጋ አንድ ወር ሆኖታል” ያለው አየር መንገዱ፤ "ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ ክልሉ በረራ አላደረግንም፤ አንድም አውሮፕላናችን በግጭቱ አካባቢ አላረፈም” ብሏል በመግለጫው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓለም አቀፉን የአየር ትራንስፖርት ማሕበርን (አይኤቲኤ) የአደገኛ ቁሶች ሕጎችን ጨምሮ ክልላዊና ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ደንቦችን በጥብቅ እንደሚከተል አስታውቋል።

አየር መንገዱ ባለው የደህንነት ጥበቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚታወቅ የገለጸው አየር መንገዱ፤ "መሬት ላይ ያለው ሃቅ ይህ ቢሆንም አንዳንድ ግለሰቦች የአየር መንገዱን ከፍተኛ ዝና ለማጠልሸት እየሠሩ ነው” ሲል ወቅሷል።

“የእኛን ስም ለማጠልሸት የተለያዩ የፎቶ ቅንብሮችን፣ የድሮ እና የማይዛመዱ ሥዕሎችን ተጠቅመዋል።" ብሏል።

“የደንብ ልብሳቸውን የለበሱ ሠራተኞች በሕዝብ ማመላለሻ መጓጓዛቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመደ ነው። ይህ ማለት ግን እኛ ወደ ውጊያ አካባቢዎች አጓጉዘናቸዋል ማለት አይደለም” ብሏል በመግለጫው።

“የሐሰት ውንጀላዎች እና ዘመቻዎች አሳሳች እና ግድየለሽ መሆናቸውን ደንበኞቻችን፣ ባለድርሻ አካላትን እና ሰፊውን ህዝብ ማሳወቅ እንወዳለን” ብሏል አየር መንገዱ።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያም ሆነ ወታደር ወደ ትግራይ አለማጓጓዙ ሊሰመርበት ይገባል ሲል አጠናቋል።