በእስር ላይ ያሉት ጋዜጠኞች አዋሽ ሰባት እንደሚገኙ ፖሊስ ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Marsaalee Hawaasaa
አካልን ነፃ የማውጣት ማመልከቻ አስገብተው የነበሩት 14 የመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞች በተመለከተ ፖሊስ ፍርድ ቤት ቀርቦ በሰጠው ምላሽ ግለሰቦቹን ወደ አዋሽ ሰባት ማዘዋወሩን ገለጸ።
ፖሊስ ለልደታ ዘጠነኛ የፍትሐ ብሔር ችሎት ትላንት ሰኞ ሐምሌ 19/2013 ዓ.ም በጽሁፍ ባቀረበው ምላሽ ተጠርጣሪዎቹ በቦታ ጥበት ምክንያት አፋር ክልል፣ ፈንታሌ ወረዳ አዋሽ ሰባት ኪሎ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ወስጃቸዋለሁ ብሏል።
ለፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት በቀረበ አቤቱታም እስከ ሐምሌ 26 ድረስ ለምርመራ ጊዜ መፈቀዱን ፖሊስ አክሏል።
ለችሎቱ በማስረጃነት የተያያዘው ለፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት የቀረበው የፖሊስ ማመልከቻ እንደሚያመለክተውም ጋዜጠኞቹ ሰኔ 29/2013 ዓ.ም የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።
ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ "በማኅበራዊ ድረ ገጽ፤ ማለትም በፌስቡክ፣ በዩቲዩብ፣ በቴሌግራም እና ዋትስአፕን በመጠቀም በውጭ አገር ከሚገኙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን፤ ሕብረተሰቡ ላይ ጫና ለመፍጠር፤ ብሔር ብሔረሰቦች እንዲጋጩ፣ ሕዝቡ ተረጋግቶ ሥራውን እንዳይሰራ፤ ጦርነት ቀስቃሽ መልዕክቶችን አሰራጭተዋል" የሚሉትን ጨምሮ በተመሳሳይ ወንጀሎች ጠርጥሬያቸዋለሁ ሲል ለፈንታሌ ወረዳ ችሎት አመልክቷል።
የመገናኛ ብዙኃን አዋጁን በመጣስ ብሎም ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የሚያስረዳው ክሱ እነዚህን ወንጀሎች ለመመርመር ጊዜ ይሰጠኝ ሲል አመልክቶ ነበር።
ሐምሌ 12 ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ሲል የጠየቀው ፖሊስ በተሰጠኝ ጊዜ ውስጥ አከናወንኩ ያላቸውን ተግባራት ዘርዝሮ ለችሎቱ አቀርቧል።
በዚህም ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን ማናገር፣ የምስክርነት ቃል መቀበል፣ ማስረጃ ማሰባሰብ፣ ከመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ማስረጃ መሰብሰብ እና ከመረጃ እና ደኅንነት የቴክኒክ ማስረጃ የመጠየቅ ሥራዎች ሰርቻለሁ ብሏል።
የቀሩ ከተባሉ ተግባራት መካከልም የተጠርጣሪዎቹን ቀሪ ግብረ አበሮች መያዝ መሆኑን ፖሊስ ለፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል በጠየቀበት ማመልከቻ ላይ ጠይቋል።
አካልን ነፃ የማውጣት አቤቱታውን ለሚመለከተው ችሎት እነዚህን ሰነዶች ያቀረበው ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያዎችን እንጂ በአፋር ክልል ፈንታሌ ወረዳ የሚገኘው ፍርድ ቤት ጊዜ ቀጠሮውን የፈቀደበትን ሰነድ አላያያዘም ተብሏል።
ችሎቱም የጊዜ ቀጠሮ የተፈቀደበት ሰነድ እንዲያያዝ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
በጉዳዩ ላይ ፖሊስ ይዞ የሚመጣውን መልስ ለመመልከትም ለፊታችን ሐሙስ ሐምሌ 22/2013 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በእስር ላይ የሚገኙት የኢትዮ-ፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞችና ሠራተኞች አያያዝ በሕግ አግባብ ሊሆን እንደሚገባው ማስታወቁ ይታወሳል።













