የፈረንሳዩ ኢማኑኤል ማክሮን ስልክ ለምስጢር መንታፊው ፔጋሰስ ተጋልጦ ነበር ተባለ

የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን

ዓለምን እያነጋገረ ያለው የስልክ ምስጢር መንታፊው ስፍትዌር፣ ፔጋሰስ የፈረንሳዩን ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ዒላማ አድርጎ እንደነበር ተነገረ።

በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ከሆነ ከ50ሺህ የፔጋሰስ ምስጢር መንታፊ ሶፍትዌር ተጠቂዎች አንዱ የማክሮን ስልክ ሆኖ ተገኝቷል።

የፈረንሳይ መንግሥት ይህ እውነት ሆኖ ከተገኘ ነገሩ በዋዛ የሚታለፍ አይሆንም ሲል አስጠንቅቋል።

ይህ እስራኤል ሰራሹ ፔጋሰስ የተሰኘ ሶፍትዌር የግለሰቦችን ስልክ በህቡእ ሰርስሮ ከገባ በኋለ አንዲት ነገር ሳያስቀር የግለሰብን ምስጢር እንደሚሰርቅ ተደርሶበታል።

ይህም የድምጽ፣ የምሥል፣ የጽሑፍና የተንቀሳቃሽ ምሥል እንዲሁም የቦታ መረጃዎችን መዝምዞ ለሦስተኛ ወገን ያቀብላል።

ፔጋሰስ መቀመጫውን እስራኤል ያደረገና በምህጻሩ ኤንኤስኦ ግሩፕ (NSO Group) በሚባል ኩባንያ የሚመረት ነው።

ከሰሞኑ ይህ ኩባንያ ዒላማ ያደረጋቸው የዓለማችን 50ሺህ ዕውቅ ሰዎች ስም ዝርዝር መገናኛ ብዙኃን እጅ ገብቷል።

ኩባንያው ግን እኔ ያጠፋሁት ነገር የለም እያለ ነው።

ይህ መንታፊ ሶፍትዌር የሚያገለግለው ለወንጀለኞችና ለአሸባሪዎች ክትትል ነው ሲል ንጹሐንን እንደማይሰልልበት ኩባንያው ተናግሯል።

የሚመረተውም በተለይ ለወታደራዊና ሌሎች የሕግ የማስከበርና የደኅንነት ሥራዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ብቻ ነው ይላል አምራቹ የእስራኤል ኩባንያ።

የፈረንሳዩ ዝነኛ ጋዜጣ ሉ ሙንድ እንደዘገበው ከሆነ ኢማኑኤል ማክሮን ከ2017 ጀምሮ ይጠቀሙበት የነበረው ስልክ በዚህ ሶፍትዌር ተጠልፎ ነበር።

ሆኖም በፔጋሰስ ዝርዝር ውስጥ መገኘት የግድ የስልክ ጠለፋ ተደርጓል ማለት እንዳልሆነና ነገር ግን ዒላማ መደረግን ብቻ ሊያሳይ እንደሚችልም ተብራርቷል።

ስልካቸው ምናልባት ተጠልፎባቸዋል ተብለው ቁጥራቸው ይፋ ከሆኑት ግለሰቦች መሀል የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ፣ የኢራቁ ባራም ሳሊህ እንዲሁም የፓኪታን፣ የግብጽና የሞሮኮ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ይገኙበታል።

የሞሮኮ ንጉሥ ስልክም በዚህ ዝርዝር ውስጥ ተገኝቷል።

የእነማን ስልክ ተጠልፎ ነበር የሚለው ዝርዝር እጃቸው ውስጥ የገባላቸው ሚዲያዎች አንድ በአንድ ስም ዝርዝሮችን እያወጡት ይገኛሉ።

ከ50ሺ ዕውቅ የዓለማችን ሰዎች መካከል የ34 አገራት 600 የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መረጃ ሲመነተፍ እንደነበር ለጊዜው ፍንጭ ተገኝቷል።