ቶኪዮ ኦሎምፒክ፡ የአትሌቲክስ ቡድን አባላት ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጁ ነን አሉ

አትሌቶች

የፎቶው ባለመብት, EAF

ከነገ ወዲያ በሚጀመረው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ውድድር ላይ ከዚህ ቀደም ከተመዘገበው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጁ መሆናቸውን አትሌቶች እና አሰልጣኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በጃፓን መዲና የሚካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ የፊታችን ዓርብ ሐምሌ 16 ጀምሮ ነሐሴ 8 ይጠናቀቃል።

ኢትዮጵያ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ከአትሌቲክሱ በተጨማሪ በውሃ ዋና፣ በብስክሌት ውድድር እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ በቴኳንዶ ውድድር ትወከላለች።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 35 አትሌቶችን ይዞ ወደ ቶኪዮ የሚያመራ ሲሆን አትሌቶች በ7 የተለያዩ ርቀቶች ተወዳዳሪ ሆነው ይቀርባሉ።

በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ የወቅቱ የ5ሺህ እና 10ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን ይዛ የምትገኘው ለተሰንበት ግደይ ትገኝበታለች።

በኮቪድ-19 ስርጭት ምክንያት በአንድ ዓመት ዘግይቶ ለሚከናወነው የኦሎምፒክ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ያለፉትን 8 ወራት በሆቴል ቆይተው ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የአትሌቲክስ ቡድኑ ዝግጅት ምን ይመስል ነበር? ሕዝቡ ምን አይነት ውጤት ይጠብቅ? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት በዝግጅት ላይ የነበሩ አትሌቶችን ጠይቀናል።

ሰለሞን ባረጋ

ሰለሞን ባረጋ አገሩን ወክሎ በ10ሺህ ሜትር ተወዳዳሪ ሆኖ ይቀርባል።

ሰለሞን ባረጋ

''ጥሩ ነጥብ እናመጣለን ብዬ አስባለሁ። እስካሁን 5ሺህ ሜትር ስወዳደር ነበር። በ10ሺህ ከእኔ ጋር ከሚወዳደሩት ጋር ተወዳድሬ ባላውቅም አሯሯጣቸውን ግን አውቃለሁ። ባለ ሪከርድ ከሆኑ የኬንያ እና ኡጋንዳ አትሌቶች ጋር ነው የምወዳደረው" በማለት አትሌት ሰለሞን ባረጋ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የ10ሺህ ሜትር ውድድር ዓርብ ሐምሌ 23 ይካሄዳል። በዚህ ውድድር ከሰለሞን ባረጋ በተጨማሪ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና በሪሁ አረጋዊ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።

አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ

የፎቶው ባለመብት, AMANUEL SILESHI

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው በ10ሺህ ሜትር ከሚወዳደሩ አትሌቶች መካከል አንዱ ነው።

ባለፉት ሁለት የኦሎምፒክ ውድድሮች ማለትም በሪዮ እና ለንደን ኦሎምፒክ በ5ሺህ እና በ10ሺህ ኦሎምፒክ የወርቅ ተሸላሚው መሐመድ ፋራህ መስፈርት ማሟላት ባለመቻሉ ከመድረኩ ቀርቷል።

ሹራ ቂጣታ

አትሌት ሹራ ቂጣታ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሎምፒክ ይወዳደራል። አትሌት ሹራ ኢትዮጵያን በማራቶችን የሚወክል ሲሆን፤ "በዚህ ውድድር ለአገርም ለግልም ወርቅ ማምጣት አለብን በሚል ነው እየተዘጋጀን ያለነው" በማለት ይናገራል።

ከአንድ ዓመት በፊት በለንደን ማራቶን የኬንያውን ኢሊዩድ ኪፕቼጌን ያሸነፈው ሹራ፤ በቶኪዮ ኦሎምፒክም የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ኪፕቼጌ ጋር ይወዳደራል።

ከአትሌት ሹራ ጋር አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ እና ሲሳይ ለማ አገራቸውን ወክለው በማራቶን ይሳተፋሉ።

አትሌት ሹራ እአአ 2020 ተካሂዶ በነበረው የለንደን ማራቶን አሸናፊ ሆኖ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ሹራ እአአ 2020 ተካሂዶ በነበረው የለንደን ማራቶን አሸናፊ ሆኖ ነበር።

አሰልጣኝ ሁሴን ሺቦ

የረዥም ርቀት ዋና አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሺቦ በኦሎምፒክ ውድድር ላይ ተሳታፊ ሲሆኑ የቶኪዮ ኦሎምፒክ 6ኛው ሆኖ ይመዘገባል።

"ለአገራችን ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ አትሌቶቻችንም፤ እኛም በአካልም በአእምሮም ዝግጁ ሆነናል" በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አሰልጣኝ ሁሴን በ5ሺህ እና 10ሺህ ሜትር ውድድሮች የሚሳተፉ አትሌቶችን ይመራሉ።

"አራት ቡድን እመራለሁ። የሴቶች እና የወንዶች 5ሺህ እና 10ሺህ ሜትር ውድድሮችን። 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን ለመያዝ አቅደን እየሰራን እንገኛለን" የሚሉት አሰልጣኙ፤ ከዚህ ቀደም ከተመዘገበ ውጤት በቶኪዮ ኦሎምፒክ ውጤት ይመዘገባል ብዬ እገምታለሁ ብለዋል።

አትሌት ለሊሳ ዴሲሳ እና ሰምበሬ ተፈሪ ከፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ሰንደቅ ዓላማ ሲረከቡ።

የፎቶው ባለመብት, Office of the President, Ethiopia

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ለሊሳ ዴሲሳ እና ሰምበሬ ተፈሪ ከፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ሰንደቅ ዓላማ ሲረከቡ።

አሰልጣኝ ሁሴን በዘንድሮ የቶኪዮ ኦሎምፒክ የሚሳተፉት አብዛኛዎቹ አትሌቶች በኦሎምፒክ ውድድር ሲሳተፉ የመጀመሪያቸው እንደሆነ ያስረዳሉ።

"ከአጠቃላይ አትሌቶች 98 በመቶ የሚሆኑት ከዚህ ቀደም በኦሎምፒክ ውድድር ተሳትፈው የሚያውቁ ስላልሆኑ በከፍተኛ ተነሳሽነት በውድድሩ ተሳትፈው አመርቂ ውጤት ያስመዘግባሉ የሚል እምነት አለኝ" ብለዋል።

ደራርቱ ቱሉ

አትሌት ደራርቱ ከሰሃራ በረሃ በታች ከሚገኙ አገራት የኦሎምፒክ ወርቅ ያገኘች የመጀመሪያዋ ጥቁር አትሌት ነች። ዘንድሮ ደግሞ ደራርቱ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንን እየመራች ወደ ቶኪዮ ታቀናለች።

"አንዳንድ ችግሮች አይታጡም ግን ዝግጅታችን በጣም ጥሩ ነው። ዓለም ለማሸነፍ ይዘጋጃል። እኛም እንደ አንድ ትልቅ አገር ለማሸነፍ ተዘጋጅተናል" በማለት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሸን ፕሬዝደንት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፉት ስምንት ወራት ፌዴሬሽኑ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ ሦስት ውድድሮችን አከናውኖ አትሌቶችን ለመመልመል እድል አግኝቷል።

"ፈጣሪ ከረዳን ጥሩ ውጤት እናመጣለን ብለን እናስባለን። እንደ ልባችን እንዳንሰራ የረበሸን ነገር ኮቪድ-19 ወረርሸኝ ነው" ብላለች አትሌት ደራርቱ።