የትራምፕ የቀድሞ አማካሪ የውጪ አገር ፍላጎትን ለማስጠበቅ ጫና አሳድረዋል ተብለው ተያዙ

ቢልየነር ቶማስ ጄ ባራክ በ2016ቱ የአሜሪካ ምርጫ ቅስቀሳ የትራምፕ አማካሪ ነበሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቢልየነር ቶማስ ጄ ባራክ በ2016ቱ የአሜሪካ ምርጫ ቅስቀሳ የትራምፕ አማካሪ ነበሩ

ለዓመታት ዶናልድ ትራምፕን የደገፉት እና የቀድሞ ፕሬዝደንት አማካሪ የነበሩት ቢልየነር ቶማስ ጄ ባራክ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ተላላኪ በመሆን ተጠርጥተው ሎስ አንጀለስ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

የ74 ዓመቱ ባራክ የኢንቨስትመንት ተቋም መስራች ሲሆኑ፤ በ2016ቱ የአሜሪካ ምርጫ ቅስቀሳ የትራምፕ አማካሪ ነበሩ። ለትራምፕ የምረጡ ዘመቻም ከፍተኛ ገንዘብ አስበሳበዋል።

ባራክ የተጠረጠሩት በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትና ከዚያ በኋላም በሕግ ወጥ መንገድ የተባበሩት አረብ አሜሬቶችን ፍላጎት ለማስጠበቅ ጫና በማሳደር ነው።

የባራክ ቃል አቀባይ እንደሚሉት፤ ባራክ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ከወንጀሉ ነፃ እንደሆኑ ይከራከራሉ።

ቢልየነሩ በአሜሪካ ክስ የቀረበባቸው የቀድሞው የትራምፕ አስተዳደር አመራሮችን ዝርዝርን ተቀላቅለዋል።

ክስ የቀረበበባቸው ተንኮል በመሸረብ፣ ፍትሕን በማስተጓጎል እና በ2019 ከኤፍቢአይ ጋር ባደረጉት ቃል ምልልስ በተደጋጋሚ በመዋሸት ነው።

ሌሎቹ ተከሳሾች የባራክ ተቀጣሪ የሆነው የ27 ዓመቱ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዜጋ ማቲው ግሪምስ እና የ43 ዓመቱ ራሺድ ሱልጣን ራሺድ አል ማሊክ አልሻሂ ናቸው።

ጊዜያዊው ተባባሪ ዓቃቤ ሕግ ማርክ ሌክሶ፤ ተጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረቡት ክሶች "አሜሪካን ከመክዳት አይተናነሱም" ብለዋል። ይህ ውንጀላ የቀድሞው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕንም ይጨምራል።

ሦስቱ ግለሰቦች የተጠረጠሩት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ፍላጎት ተፈጻሚ ለማድረግ የትራምፕ ባለሥልጣኖች ላይ ጫና በማሳደር ነው። በተጨማሪም መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ለአረብ ኤምሬቶች የሚወግን መረጃ አሰራጭተዋል ተብሏል።

2016 ላይ ባራክ አረብ ኤምሬቶችን የሚያወድስ ጽሑፍ በትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ንግግር እንዲካተት አድርገዋል ተብሏል።

የዚህ ጽሑፍ ረቂቅ በሌላው ተከሳሽ አልሻሂ በኩል ለአረብ ኤምሬቶች ባለሥልጣናት እንዲደርስ ተደርጓል።

ሦስቱ ግለሰቦች ከአረብ ኤምሬቶች "በመገናኛ ብዙኃን ንግግር ሲደረግ የሚነሱ ነጥቦች" እንደተቀበሉም ተመልክቷል።

በቀረበባቸው የክስ ሰነድ ላይ "ባራክ አንድ ንግግር አድርገው ከጨረሱ በኋላ ለአልሻሒ በጻፉት ኢሜል 'ለቡድናችን ድል አስመዝግበናል፤ አሳክቼዋለሁ' ብለዋል። ቡድን የሚለው ቃል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ይጠቁማል" ይላል።

በአቡ ዳቢ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የሚመረጡት ግለሰብ በአረብ ኤምሬቶች የሚመረጡ እንዲሆኑም ጫና አሳድረዋል።

ከ2016 ምርጫ በኋላ ባራክ ሌሎቹ ሁለት ተከሳሾች የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ውስጥ እንዲካተት የምትፈልገውን እንዲጽፉ መጠየቃቸውን ክሱ ይጠቁማል።

ባራክና ማቲው ካሊፎርንያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ቢውሉም፤ አልሻሂ ግን እስካሁን አልተያዙም።