የአውሮፓ ሕብረት ሱዳንን እንዲያወግዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ

የፎቶው ባለመብት, The Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia
ከድንበር ውዝግቡ ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ሕብረት ሱዳንን በጠብ አጫሪነት ማውገዝ አለበት ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጥሪ አቀረበ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ከውግዘቱ በተጨማሪ የድንበር ውዝግቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ መንገዱን ለማመቻቸት ሱዳን ከትግራይ ጦርነት በፊት ወደነበረው ወደቀደመ ስፍራዋ እንድትመለስ ጥሪ እንዲያደርግ ሕብረቱን ጠይቀዋል።
ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አኔት ዌበር ጋር በትናንትናው ዕለት ባደረጉት ውይይት ላይ መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
ሁለቱ ባለስልጣናት የኢትዮ-ሱዳንን የድንበር ግጭት አስመልክቶ ባደረጉት ውይይት ሱዳን የግዛት ይገባኛል ጥያቄዋን በኃይል ለመፍታት ሞክራለች ብለዋል።
ይህም ሁኔታ የዓለም አቀፍ ሕግ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት መርሆዎችና ዓላማዎችን የጣሰ እንደሆነም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለልዩ ተወካይዋ ተናግረዋል።
የሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት በድንበር አካባቢ በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ይዞታ ስር የነበሩ በርካታ ስፍራዎችን ሠራዊታቸው በቁጥጥር ስር ማስገባቱን የገለጹ ሲሆን፤ በዚህ ሳቢያ በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውንና ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መውደሙን በኢትዮጵያ በኩል መገለጹ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የትግራይ ጦርነትን ተከትሎ ሱዳን ያላግባብ "የወረረችውን መሬት" ትልቀቅና ወደ ንግግር እንግባ ብትልም ሱዳን በበኩሏ ሠራዊቱ ግዛቴ ነው ከሚላቸው ቦታዎች ውስጥ አብዛኛውን መቆጣጠሩንና ይህም የማይቀለበስ እርምጃ መሆኑን መግለፃቸው የሚታወስ ነው።
ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዝግብ በተጨማሪ ልዑኳና ሚኒስትሩ ስለ ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ፣ የሕዳሴ ግድብ ሙሌትና የሦስትዮሽ ድርድርና የመንግሥትን የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅን በተመለከተም መወያየታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ኢትዮጵያ በቅርቡ የተጠናቀቀው አጠቃላይ ምርጫ ሰላማዊና ተአማኒነት የነበረው ነው" በማለት የተሳካ ነው ብለውታል።
በተጨማሪም የፌደራል መንግሥቱ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት ለመስራት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መቀየሱን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የተናጠል ተኩስ አቁሙን በተመለከተ የመንግሥታቸውን አቋም አስረድተዋል። መንግሥት ለተሻለ የሰብዓዊ አቅርቦት ተደራሽነት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በቅርበት ለመስራት እና የትግራይ ክልልን መልሶ ለማቋቋም ነውም ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሓት ኅብረተሰቡን እንደ ሰብአዊ ጋሻ አድርጎ በመጠቀም፣ ወታደራዊ ጥቃቶችን በመፈፀም፣ የሰብዓዊ ድጋፍን በማደናቀፍ እንዲሁም ህፃናትን በወታደርነት በመልመል የተኩስ አቁሙን ጥሷል ብለውታል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ደመቀ እንዳሉት የአንድ ወገን ሰብአዊ የተኩስ አቁም ስምምነትን በሚያደናቅፍ ላይ የፌዴራል መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጸዋል።
ህወሓት በስምምነት ላይ የተደረሰ የተኩስ አቁም እንደሚቀበል ያስታወቀ ሲሆን ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ከክልሉ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቀው ይገኝበታል።
ባለፉት ወራት ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲመረመሩ እንዲሁም ቴሌኮም፣ መብራትና የአውሮፕላን በረራን ጨምሮ የተቋረጡ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲጀመሩም ጠይቋል።
ከዚህም በተጨማሪ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች ህወሓት ህፃናትን በወታደርነት እያሰማራ ይገኛል ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ህወሓት "ሕጻናትና ወጣቶችን በአደንዛዥ ዕጽ እያሳበደ ወደ ጦርነት እየማገደ ይገኛል" በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፅሁፋቸው መግለፃቸው የሚታወስ ነው።
ይህንንም አስመልክቶ ህወሓት ከቀናት በፊት በሰጠው ምላሽ ዓለም አቀፍ ፕሮቶኮሎች ከሚያዙት ውጭ ከእድሜ በታች የሆኑ ህፃናት አልተሳተፉም ብሏል።
ከሰሞኑ ኒው ዮርክ ታይምስ 'የትግራይ ኃይሎች የፌደራሉን መንግሥት ጦር ከትግራይ ያስወጡበት መንገድ' ብሎ በሰራው ዘገባ ውስጥ የተካተቱት ምስሎች ተዋጊዎችን ሊቀበሉ የወጡና ጦርነት በሌበት ሁኔታ ነው ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የአውሮፓ ሕብረት የትግራይ ክልልን በተመለከተ ለተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አቅርቦ ያጸደቀውን ውሳኔንም በማንሳት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜውን ያልጠበቀና የፖለቲካ አላማ ያለው ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን እና የተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን በጋራ የሚያደርጉትን ምርመራም ከግምት ያላስገባ ነው ሲሉም ወቅሰዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ሰብሰባ ላይ የአውሮፓ ሕብረት ከትግራዩ ግጭት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደሚያሳስበውና የኤርትራ ሠራዊት አባላት ከትግራይ በአስቸኳይ እንዲውጡ በመጠየቅ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ተቀባይነት ማግኘቱ የሚታወስ ነው።
ልዩ ተወካይዋ በበኩላቸው በትግራይ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የሚደረገው የጋራ ምርመራ የተፋጠነ እንዲሆን መጠየቃቸው ሰፍሯል።
ከዚህም በተጨማሪ በትግራይ ክልል ሊፈጠር የሚችለውን የሰብዓዊ ቀውስ ለአውሮፓ ሕብረት ስጋት እንዳጫረበት ልዩ ልዑኳ ገልፀዋል።
በመጨረሻም ኢትዮጵያ ለቀጠናው መረጋጋት ሚና እንዳላት የአውሮፓ ሕብረት እንዲረዳ እና አላስፈላጊ ጫና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከማሳረፍ ይልቅ በአዎንታዊ መልኩ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ አቶ ደመቀ ጥሪ አቅርበዋል።












