"በሙሉ ጤንነት ላይ ነኝ" ጄነራል ብርሃኑ ጁላ

የፎቶው ባለመብት, ENA/SCREEN GRAB
ከረጅም ጊዜ በኋላ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በኩል የቀረቡት የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ጠፍተው የቆዩት በሥራ መብዛት ምክንያት እንጂ በሙሉ ጤንነት ላይ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።
በተለይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ የማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ከፍተኛ የጤና መታወክ ገጥሟቸዋልና ሌላም የሚሉ ወሬዎች ሲናፈሱ ቆይተዋል።
በኢዜአ ሰኞ ዕለት መቅረባቸውን ተከትሎ ቢቢሲ ያናጋራቸው ጄነራሉ ከዕይታ ርቀው የቆዩት በከፍተኛ የሥራ ጫና ውስጥ መቆየታቸውን ጠቅሰው በጤና በኩል ምንም እክል እንዳልገጠማቸው "መቶ በመቶ በመልካም ጤንነት ላይ ነኝ" ሲሉ ተናግረዋል።
ጄነራል ብርሃኑ እሳቸውን በተመለከተ ሲናፈስ ስለቆየው ጉዳይም "ሰው በሃሳብ ሲለያይ እና በጠላትነት ሲተያይ ጠላቴ ነው ላለው ወገን መልካም ነገር አያስብም። ይሄ ከእኛ ጋር እየተፋለሙ ያሉ ኃይሎች እና ወዳጆቻቸው ምኞት ነው። የጤናዬን ጉዳይ ከእኔ በላይ የሚያውቅ ጠንቋይ ያለ አይመስለኝም። ራስ ምታት እንኳን የለኝም" አጣጥለውታል።
ረዘም ካለ ግዜ በኋላ በመገናኛ ብዙሃን ትናንት ቀርበው በሰጡት መግለጫ ጄነራል ብርሃኑ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከነዚህም መካከል ሠራዊቱ ከትግራይ ክልል የወጣበት ምክንያት ብሎም ሊመለስ ስለሚችልባቸው ነጥቦች ጥቆማ ሰጥተዋል።
"ከትግራይ እና ከመቀለ የወጣነው መንግሥት በወሰነው ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው። ውሳኔውም ትክክል ነው ብለን እናምናለን። እዲሁም ለትግራይ ሕዝብ ሲል የከፈለው ዋጋ ነው ብለን እናምናለን። ያንን ግዳጅ ተቀብለን ነው የወጣነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
ከስምንት ወራት ውጊያ በኋላ ሠራዊቱ እረፍት እያደረገ ብሎም መልሶ እየተቋቋመ እንደሆነ የጠቆሙት ጄነራሉ ስልጠና እና የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ እደሆነ አመልክተዋል።
"ዝግጅታችንን በከፍተኛ ሁኔታ እያጠናቀቅን ነው። መንግሥት ለሚሰጠን ግዳጅ ዝግጁ ሆነን በመጠበቅ ላይ ነን" ሲሉም አክለዋል።
ጨምረውም አማጺው ኃይል "ማዕከሉ ሕዝብ ከሆነ የትግራይን ሕዝብ እስከዛሬ ያሰቃየው ስለሚበቃ ቆም ብሎ አስቦ መንግሥት ያመቻቸውን የተናጠል ተኩስ አቁም ተቀብሎ፤ እርሱም ተኩስ አቁሞ የሚፈልገው የፖለቲካ ጥያቄ ካለ መደራደር እንዳለበት እንመክራለን" ብለዋል ኤታማዦር ሹሙ።
"በቅድመ ሁኔታ የተሽቆጠቆጠ ሰላም አይመጣም፣ ማንም ቅድመ ሁኔታ ደርድሮ 'እዚህ ውስጥ ግባ እና ነው የምንደራደረው' የሚል ካለ ማንም እሺ አይልም። አንድ ነገር ስታደርግ ሌላው ምን ያደርጋል የሚለውን ማሰብ ጥሩ ነው" ሲሉ ጠቁመዋል።
ጄነራል ብርሃኑ አክለውም ነገሮች በጉልበት የሚቀጥሉ ከሆነ "የመከላከያ ሠራዊት ጦርነቱን ስንጀምር ከነበረው ደረጃ በላይ ጠንካራ፣ የውጊያ ልምድ ያለው ብሎም በደንብ የታጠቀ ነው፤ የመንግሥትን ትዕዛዝ ነው የሚጠብቀው። አሁን ባለው ሁኔታ የሚቀጥሉ ከሆነ እንደለመድነው ማድረጋችን አይቀርም" ሲሉ ተደምጠዋል።
ሠራዊቱ በመንግሥት ስር የሚኖር እንደሆነ የገለጹት ጄነራል ብርሃኑ "ውጣ ስንባል እንወጣለን፤ ግባ ስንባል እገባለን" ብለዋል።
ህወሓት በስምምነት ላይ የተደረሰ የተኩስ አቁም እንደሚቀበል ያስታወቀ ሲሆን ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ከክልሉ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቀው ይገኝበታል።
ባለፉት ወራት ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲመረመሩ እንዲሁም ቴሌኮም፣ መብራትና የአውሮፕላን በረራን ጨምሮ የተቋረጡ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲጀመሩም ጠይቋል።
የህወሓት ኃይሎች ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝን ማጥቃታቸውን ተከትሎ በትግራይ ክልል ውስጥ ወታደራዊ ግጭት መቀስቀሱ ይታወሳል።
ከስምት ወራት ቆይታ በኋላ የፌደራል መንግሥት የክረምቱን የእርሻ ጊዜ ምክንያት በማድረግ የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ከትግራይ ክልል ማስወጣቱን አሳውቋል።
የህወሓት ኃይሎች በበኩላቸው የተኩስ አቁም ለማድረግ ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርበው እስካልተሟሉ ድረስ ከስምምነት እንደማይደርሱ አሳውቀዋል።
ይህንንም ተከትሎ በአማራ እና በትግራይ ድንበሮች አካባቢ ባሉ ስፍራዎች ወታደራዊ ግጭቶች የተካሄዱ ሲሆን ከሳምንት በፊት አማጺያኑ አላማጣና ኮረምን መቆጣጠራቸው ተዘግቧል።
የፌደራሉ መንግሥትም ጥቃቱ የሚቀጥል ከሆነ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ገልጿል። ጄነራል ብርሃኑ ጁላም ሠራዊታቸው የመንግሥትን ትዕዛዝ እየተጠባበቀ መሆኑን ተናግረዋል።














