ወደ ትግራይ እርዳታ ጭነው ሲሄዱ የነበሩ 10 ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ተፈጸመባቸው

የተራበ ህፃን ልጅ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ወደ ትግራይ እርዳታ ጭነው ሲጓዙ በነበሩ አስር ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለጸ።

ይህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የተራቡ የክልሉ ነዋሪዎችን ለመርዳት የበለጠ አዳጋች ሁኔታን እንደፈጠረም የዓለም ምግብ ፕሮግራም አመልክቷል።

ሰብዓዊ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ እየሄዱ የነበሩት 10 ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃቱ የደረሰው በአፋር ክልል ከሰመራ 115 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ስፍራ እሁድ ዕለት መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም በመግለጫው አስታውቋል።

"አስፈላጊ የሚባሉ ሰብዓዊ እርዳታዎችን ጭነው ወደ ትግራይ ክልል ለመግባት ሲሞክሩ ነው ጥቃቱ የደረሰው" ብሏል ድርጅቱ።

በተሽከርካሪዎቹ ላይ ማን ጥቃት እንዳደረሰ እስካሁን የተገለፀ ነገር የለም።

ከአደጋው በስተጀርባ ማን እንዳለ ለማጣራት ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር እየሰራ መሆኑንም ድርጅቱ ማሳወቁን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

"የአካባቢው ደኅንነት እስኪረጋገጥና አሽከርካሪዎቹም በሰላም መጓዝ እንደሚችሉ እስኪረጋገጥ ድረስ ሁሉም የእርዳታ ጉዞዎች ታግዷል" ብሏል የዓለም ምግብ ፕሮግራም።

በሰኔ ወር መጨረሻ ሁለት ቁልፍ ድልድዮች መውደማቸውን ተከትሎ በሰመራ በኩል ወደ ትግራይ የሚወስደው መስመር ለእርዳታ አቅርቦት ወሳኝ መዳረሻ መንገድ ሆኗል።

ነገር ግን ከስምንት ወራት በላይ የቀጠለው ጦርነት ወደ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ተዛምቶ ከሰሞኑም ወደ ትግራይ ለሚደረገው የሰብዓዊ እርዳታ አገናኝ በሆነችው አፋር ክልል ውጊያ ተከስቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) በበኩሉ በባለፈው ወር በትግራይ ውስጥ ያሉ ስፍራዎች ተደራሽነት የተሻሻለ ቢሆን ወደ ክልሉ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ክልከላ የሰብዓዊ እርዳታው ላይ መስተጓጎል ፈጥሯል ብሏል።

ድርጅቱ በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል ቀደም ሲል ለመድረስ አስቸጋሪ የነበሩ አካባቢዎችን ተደራሽ ሆነዋል ብሏል።

በክልሉ ከ5.2 ሚሊዮን 4 ሚሊዮን የሚሆኑት ወይም 75 በመቶዎቹን እርዳታ ፈላጊዎች ማግኘት እንደተቻለም አስታውቋል።

ይህም በግንቦት ወር 30 በመቶ ከነበረው የተሻለ እንደሆነም በመግለጫው አመልክቷል።

ሆኖም ግን የሰብዓዊ እርዳታ ክምችት እየተመናመነ ነው ሲል ስጋቱን ገልጿል።

ወደ ትግራይ ለመድረስ ብቸኛው መንገድ አፋር መሆኑም በአሁኑ ወቅት ውጊያ በስፍራው መከሰቱም ለሰብዓዊ እርዳታ ፈታኝ አድርጎታል ብሏል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለትግራይ ክልል የላካቸው ሰብዓዊ እርዳታ ጭነት መቀለ መግባታቸው ተገልፆ ነበር።

ለመጀመሪያ ጊዜ የደረሰው ይህ እርዳታ በ50 የጭነት መኪኖች የተጓጓዘ ሲሆን በመቀለ የደረሰው እርዳታ 900 ሜትሪክ ቶን ምግብና አስፈላጊ ቁሳቁስ ቢሆንም በክልሉ ካለው ችግር አንፃር ይህ ቁጥር በእጥፍ ማደግ አለበት ተብሏል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለሰብዓዊ እርዳታ በረራ ለማካሄድ በጠየቀው መሰረት ከመንግሥት ፈቃድ ፍቃድ ማግኘቱን ተከትሎ ቅዳሜ ዕለት ወደ ትግራይ የሙከራ በረራ በተሳካ ሁኔታ ማካሄዱን አስታውቋል።

መደበኛ በረራዎች ከሐምሌ 14/2013 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚጀምሩም አስታውቋል።