በአፋር እና ትግራይ አዋሳኝ ድንበር ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተነገረ

የህወሓት አማጺያን በአፋር እና ትግራይ አዋሳኝ ድንበር ላይ በፌደራሉ መንግሥት ጎን በተሰለፉ ኃይሎች ላይ ተኩስ መክፈታቸው ተሰማ።
የፌደራሉ መንግሥት እና የአፋር ክልል መንግሥት ከሁለት ቀናት በፊት ባወጡት መግለጫ የህወሓት አማጺያን በአፋር ክልል በኩል ተኩስ መክፈታቸውን አመልክተዋል።
መንግሥት በአፋር በኩል ወደ ትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ ሲጓጓዝ የህውሓት ቡድን አካባቢውን በከባድ መሳሪያ በመደብደብ መንገድ ዘግቷል ሲል የአፋር ክልል መንግሥት ደግሞ የህውሓት ቡድን በያሎ ተብሎ በሚጠራው ወረዳ በኩል ተኩስ መክፈታቸውን ገልጿል።
የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ በተገቢው መልኩ ለማዳረስ የተናጥል ተኩስ ማቆሙን አስታውሶ፤ ቅዳሜ ዕለት በአፋር በኩል ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን የጫኑ 60 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል እየተጓዙ ሳለ የህወሓት አማጺያን ተኩስ በመክፈት እንዳይጓጓዝ መንገድ ዘግቷል ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የህውሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በአፋር ክልል በኩል በነበሩ ለፌደራሉ መንግሥት በወገኑ ኃይሎች ላይ ወታደራዊ ርምጃ ወስደናል ሲሉ ትናንት ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ጌታቸው ረዳ "የተገደበ" ያሉት ወታደራዊ እርምጃ በአፋር በኩል ተሰልፎ በነበረው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ላይ ያነጣጠረ እንደነበረ ተናግረዋል።
"እነዚህን እርምጃዎች የወሰድነው ይህ ኃይል ወደ ኦሮሚያ እንዲመለስ ነው፤ ይህን ማድረግም ችለናል" ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። በህወሓት አማጺያን በተሰነዘረው ጥቃት የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲመለስ ስለመደረጉ በገለልተኛ አካል አልተረጋገጠም።
ባለፉት ሳምንታት የህወሓት አማጺያንን ለመውጋት የበርካታ ክልል ኃይሎች ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ መንቀሳቀሳቸው ይታወሳል። ከፌደራሉ መንግሥት ጎን ከተሰለፉት መካከል የኦሮሚያ፣ የሶማሌ፣ የሲዳማ፣ የደቡብ፣ ቤኒሻንጉል እና ሐረሪ ይገኙበታል።
የአፋር ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም ቅዳሜ ዕለት ጋዜጠኞችን ሰብስበው ፈንቲ ረሱ ዞን በያሎ ወረዳ በኩል ጦርነት መክፈቱን አመልክተው የህወሓት አማጺያን በክልሉ ሊያደርሱ ከሚችሉት ጥቃት ሕዝቡ ራሱን በንቃት መጠበቅ አለበት በማለት አሳስበዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የክልሉን የፀጥታ ሀይል ለመቀላቀል ፍላጎት ያላቸው በተለይም የወታደራዊ ልምድ ያላቸው አካላት ፖሊስ ኮሚሽን በመቅረብ ምዝገባ እንዲያደርጉ ኢብራሂም ሁመድ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኢብራሂም ሁመድን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ የህወሓት አማጺያን ቅዳሜ ጠዋት አደረሱት በተባለው ጥቃት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

ከወራት በፊት የተቀሰቀሰው ጦርነት ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት እንዳደረሰ ቢነገርም አስካሁን ከየትኛውም ወገን ይህ ነው የሚባል ዝርዝር መረጃ አልወጣም።
ለስምንት ወራት የተካሄደውን ጦርነት ለማብቃት የፌደራል መንግሥቱ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱ ይታወሳል።
አማጺው ኃይል በበኩሉ በድርድር ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም ለማድረግ ሰባት ነጥቦችን የያዘ ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርቧል።
በህወሓት አማጺ በኩል እንደ ቅድመ ሁኔታ ከተቀመጡ ጉዳዮች መካከል ደግሞ አንዱ በትግራይ እና አማራ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎች ይለቀቁ የሚለው ይገኘበታል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ጸ/ቤት ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው ስፍራዎች የክልሉ መንግሥት ለቅቆ እንደማይወጣ አስታውቋል።












