ነዳጅ አምራች አገራት የነዳጅ ዋጋን ለመቀነስ ከስምምነት ደረሱ

ነዳጅ ማውጫ ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ነዳጅ አምራች አገራት የነዳጅ ዋጋን ለመቀነስ እና በዓለም ምጣኔ ሃብት ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማቃለል ምርታቸውን ለማሳደግ ተስማሙ።

በሁለት ዓመት ተኩል ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ዋጋዎች ከጨመሩ በኋላ የነዳጅ ላኪ አገራት ድርጅት (ኦፔክ) አባላት እና እንደ ሩሲያ ያሉ ከድርጅቱ ውጭ ያሉ አገራት ከነሐሴ ጀምሮ አቅርቦትን ያሳድጋሉ።

እርምጃው የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ላይም ተጽዕኖ ይኖረዋል ተብሏል።

የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በዚህ ዓመት በ43 በመቶ ገደማ ጨምሮ በበርሜል ወደ 74 ዶላር ከፍ ብሏል።

ባለፈው ዓመት ኦፔክ እና አጋሮቻቸው በወረርሽኙ የተነሳ የፍላጎት ማሽቆልቆል በመኖሩ እና ዋጋው በመቀነሱ ከምርታቸው በቀን 10 ሚሊዮን በርሜል ቀንሰው ነበር።

ይሁን እንጂ በዚህ ዓመት የዓለም ምጣኔ ሃብት እያንሰራራ በመሆኑ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል። ይህም በአንዳንድ አገራት የዋጋ ግሽበት እንዲጨምር አስተዋጽኦ በማድረጉ እና በዓለም የኢኮኖሚ መሻሻል ላይ እንቅፋት እንዳይሆን አስግቷል።

የነዳጅ አምራቾች ዋጋ ለመቀነስ ፍላጎት ቢያሳዩም በሳዑዲ አረቢያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በሐምሌ ወር መጀመሪያ ዕቅዱን እንዲደናቀፍ ምክንያት ሆኗል።

በሪያድ እና በሞስኮ የቀረበውን ተጨማሪ ነዳጅ የማምረት ዕቅድ ፍላጎት አቡዳቢ ውድቅ አድርጋ ነበር።

በቅርብ አጋሮች መካከል ያልተለመደ ውዝግብ ከ50 በመቶ በላይ የነዳጅ አቅርቦቶችን የሚቆጣጠረውን ኦፔክና አጋሮቹ መረጋጋት ላይ ጥያቄ አስነስቷል።

በአዲሱ ስምምነት መሠረት ኦፔክ እና አጋሮቹ ገበያውን ለማረጋጋት ከነሐሴ እስከ ታህሳስ 2021 ድረስ በቀን ተጨማሪ ሁለት ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ለማምረት ተስማምተዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሩሲያ፣ ኩዌት እና ኢራቅን ጨምሮ በርካታ አባል ሃገራት ከግንቦት 2022 ጀምሮ ከፍተኛ የምርት ኮታ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

ባለፈው ዓመት ወደ ሥራ የገባው የነዳጅ ምርት ቅነሳ እስከ መስከረም 2022 ድረስ ያበቃል ብሏል።

የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ኖቫክ አባላቱ "ገንቢ" እና "መግባባት" ላይ ደርሰዋል ብለዋል።

"ወረርሽኙ እስካ አሁን በቁጥጥር ስር ባይውልም በመላው ዓለም በክትባት ምክንያት እንደ መኪኖች እና የአውሮፕላን ነዳጅ በመጨመሩ ምርታችን እያገገመ መሆኑን እያየን ነው" ብለዋል።

"ኃላፊነታችንን መወጣት እና የዓለም ኢኮኖሚ እንዲረጋጋ ማድረግ በጣም አስፈላጊያችን ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡