ሱዳንና ግብፅ ወደ ሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲመለሱ ኢትዮጵያ ጠየቀች

ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብፅ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ወደሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር እንዲመለሱ ጠይቃለች።

ኢትዮጵያ ይህንን ጥያቄ ያቀረበችው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት በኩል በዛሬው ዕለት ባወጣችው መግለጫ ነው።

በሶስቱ አገራት መካከል የሚደረገው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር፣ ሦስቱ አገራት ከዚህ ቀደም የተፈራረሙትን የመርሆዎች ስምምነትን መሠረት ባደረገ መልኩ የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት እና ኦፕሬሽንን በተመለከተ ከስምምነት ላይ ለመድረስ ወይይት ሲደረግ መቆየቱን የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውሷል።

ነገር ግን ከዚህ ተቃራኒ ድርድሩ እየተጓተተና ፖለቲካዊ አውድ ሲሰጠው ኢትዮጵያን ማሳዘኑን መግለጫው አስፍሯል።

ኢትዮጵያ ድርድሩን በዚህ መልክ መውሰዱ ፍሬያማ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ መናገሯን ያሰመረው መግለጫው ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት መውሰዱ ጥቅም የሌለውና ከምክር ቤቱም ስልጣን የራቀ ነው ብሏል።

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መጀመሯን ተከትሎ ግብፅ የቀጠናውን መረጋጋት አደጋ የሚጥል ነው በማለት እርምጃውን መቃወሟ የሚታወስ ነው።

ለአመታት ያህል በግብፅ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ሲደረግ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር ፍሬ ሳያፈራ የቀረ ሲሆን ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌቱን ተከትሎ ግብፅና ሱዳን ጉዳዩን ወደ ተመድ የፀጥታ ጉባኤ ምክር ቤት ወስደውት ነበር።

በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ሲደረግ የነበረው ድርድር ምንም ፍሬ አላፈራም ሲሉም ነበር ወደ ምክር ቤቱ ጉዳዩን የወሰዱት። ምክር ቤቱ የህዳሴ ግድብን ውዝግብ ከተለያዩ ወገኖች ከሰማ በኋላ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመለሱ ምክር ለግሶ ልኳቸዋል።

መግለጫው በተጨማሪም በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚደረገውን ፋይዳም ጠቅሷል።

በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚደረገው ድርድር እያንዳንዱ ወገን የሚያሳስባቸውን ነገሮች ለመቅረፍ ጠቃሚ የሆነ መድረክ እንደሆነም መግለጫው ጠቅሶ በዚህም ሂደት በብዙ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መደረስ እንደተቻለም አትቷል።

በተጨማሪም ይህ ሂደት በናይል ወንዝ ላይ የውሃ ስምምነት እና በተፋሰሱ አሰራር ባለመኖሩ ምክንያት የቆዩ ተግዳሮቶችንም ይፋ እንዳደረገ አስፍሯል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሶስትዮሽ ድርድር በጋራ ተቀባይነት ያለው ውጤት እስኪደረስና ስኬታማ እንዲሆንም ቁርጠኛ ናት ብሏል።

በአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር በቀረበው አሰራር ላይ ለመስራት ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን ገልፆ ግብፅና ሱዳንም ሂደቱን ወደ ፍሬ ለማምጣት በቅን ልቦና እንዲደራደሩም ጠይቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ሁሉንም አካላት ተጠቃሚ የሚያደርግ መፍትሔ እንዲገኝ እንደሚሠራ የተመድ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ፓርፋይት ኦናንጋ አንያንጋ መግለፃቸው የሚታወስ ነው።

ልዑኩ "የተባበሩት መንግሥታት በጉዳዩ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በአጠቃላይ የሚስማሙበትን መንገድ ለመቀየስ ዝግጁ ነው" ማለታቸውን ድርጅቱ የሕዳሴው ግድብን በተመለከተ በጸጥታው ምክር ቤት ውይይት ከተካሄደ በኋላ ባወጣው መግለጫ ላይ ተመልክቷል።

አባል አገራቱ ይህንን ውስብስብ ጉዳይ በፖለቲካዊ መልካም ፍቃደኝነት ላይ ተመርኩዘው እንዲሁም አንዳቸው የሌላኛውን ፍላጎት ሳይጫኑ መፍትሔ እንዲገኝ እንደሚፈለግ ልዑኩ ገልጸዋል።