የተባበሩት መንግሥታት በግድቡ ዙሪያ ሁሉንም የሚያስማማ መፍትሔ እንዲገኝ እጥራለሁ አለ

የተባበሩት መንግሥታት ታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ሁሉንም አካላት ተጠቃሚ የሚያደርግ መፍትሔ እንዲገኝ እንደሚሠራ የተመድ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ፓርፋይት ኦናንጋ አንያንጋ ማለታቸው ተገለጸ።

ልዑኩ "የተባበሩት መንግሥታት በጉዳዩ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በአጠቃላይ የሚስማሙበትን መንገድ ለመቀየስ ዝግጁ ነው" ማለታቸውን ድርጅቲ የሕዳሴው ግድብን በተመለከተ በጸጥታው ምክር ቤት ውይይት ከተካሄደ በኋላ ባወጣው መግለጫ ላይ ተመልክቷል።

አባል አገራቱ ይህንን ውስብስብ ጉዳይ በፖለቲካዊ መልካም ፍቃደኝነት ላይ ተመርኩዘው እንዲሁም አንዳቸው የሌላኛውን ፍላጎት ሳይጫኑ መፍትሔ እንዲገኝ እንደሚፈለግ ልዑኩ ገልጸዋል።

ልዑኩ አያይዘውም በአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት እየተካሄደ ያለው ውይይት እምብዛም ለውጥ እያመጣ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ፣ በግብጽ እና በሱዳን መካከል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ የሚደረገውን የሦትስዮሽ ድርድር የአፍሪካ ሕብረት እየመራው ነው። ሆኖም ግን ሦስቱ አካላት ችግራቸውን የሚፈቱበት መንገድ እንዳላገኙ ተገልጿል።

ይህም በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት የሚፈቱበት መንገድ አለማግኘታቸውን እንዲሁም ድርቅ ቢከሰት ከግድቡ አንጻር ምን ይደረጋል? የሚለው ላይ አለመስማማታቸውን ያካትታል።

ታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ውዝግብ ውስጥ ከገቡ ወደ አሥር ዓመታት ተቆጥረዋል።

ሱዳን እና ግብጽ በጉዳዩ ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲመክር ጥያቄ አቅርበው ሐሙስ ዕለት ውይይት ተደርጓል።

የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን "አገራት የሚጋሩት የውሃ ሀብት የግጭት መንስኤ ሲሆኑ ታይቷል። ከዚህ በተቃራኒው የትብብር መነሻ መሆን ይችላሉ" ሲሉ ለአገራቱ አምባሳደሮች ተናግረዋል።

"ሌሎች ግጭት የሚያጭሩ ነገሮች በቀጠናው በበዙበት በዚህ ወቅት ልዩነቶችን ለመፍታት ጥንቃቄ የተሞለው እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል" ሲሉ ተናግረዋል።

አገራቱ ወደ ስምምነት እንዲመጡ የቴክኒክ እንዲሁም የሕግ ጉዳዮች አማካሪ ድጋፍ እንዲሰጡም አሳስበዋል።

ሦስቱ አገራት ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ እንዲሆኑ የጠየቁት ኢንገር አንደርሰን "ሦስቱ አገራት በትብብር መፍትሄ ማግኘት አለባቸው። አንድ ወንዝ፣ አንድ ሕዝብ፣ አንድ አላማ በሚል መርህ ለጋራ እድገት መሥራት አለባቸው" ሲሉም አክለዋል።

ኢንገር አንደርሰን ግድቡን በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል እና መቻል እንዳለበትም በአጽንኦት ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሦስቱንም አገራት ተጠቃሚ በሚያደርግ መፍትሔ ላይ እንዲደረስ እንደሚደግፍ አክለዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት ድጋፍ ለአፍሪካ ሕብረት ጭምርም እንደሆነም አስረድተዋል።

የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተማ እና የኢንዱስትሪ መስፋፋት የውሃ ፍላጎት እንዲጨምር ማድረጉን ከግምት በማስገባት ሦስቱ አገራት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሁን መተባበር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

"የጎርፍ አደጋ ስጋት ከምንጊዜውም በላይ እየጨመረ ነው። በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የድርቅ ስጋትም ስላለ የሦስቱ አገራት ትብብር ያስፈልጋል" ብለዋል።

ሦስቱ አገራት ችግራቸውን በጋራ መፍታታቸው የግድ እንደሚሆን ገልጸው፤ "ስምምነት ላይ ለመድረስ መተማመን፣ ግልጽ ውይይት ያስፈልጋል" ሲሉም አክለዋል።