ታሊባን በአፍጋኒስታን የሚቀር የውጪ ኃይል እንዳይኖር አስጠነቀቀ

የአፍጋኒስታን ጦር አባል

የፎቶው ባለመብት, EPA

በአፍጋኒስታን የሚቀር የውጪ ኃይል እንደ ወራሪ ጠላት እንደሚታይ ታሊባን አስታወቀ።

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እስከ መስከረም ድረስ አፍጋኒስታንን ለቆ ለመውጣት ባስቀመጠው ቀነ ገደብ መሠረት ለቆ የማይወጣና በአፍጋኒስታን የሚቀር ማንኛውም የውጪ አገር ሠራዊት እንደ ጠላት እንደሚታይ ታሊባን አስጠንቅቋል።

ይህ የታሊባን ማስጠንቀቂያ የመጣው ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎችን እና የካቡልን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለመጠበቅ አንድ ሺህ የአሜሪካ ወታደሮች ሊቆዩ እንደሚችሉ መረጃ ከወጣ በኋላ ነው።

ኔቶ በአፍጋኒስታን ለ20 ዓመታት የዘለቀውን ወታደራዊ ተልዕኮ አጠናቋል። ነገር ግን ታሊባን ተጨማሪ ግዛቶችን እየተቆጣጠረ በመምጣቱ በአገሪቱ ውስጥ ሁከት እየጨመረ መጥቷል።

የአፍጋኒስታን ኃይሎች የአገሪቱን ጸጥታ ለብቻቸው ለመቆጣጠር እየተዘጋጁ ባሉበት በዚህ ወቅት የካቡል የወደፊት ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

የታሊባን ቃል አቀባይ ሱሃይል ሻህን ካቡልን በጦር ኃይል መያዝ "የታሊባን ፖሊሲ አይደለም" ካሉ በኋላ፤ ኳታር ውስጥ ከሚገኘው የታጣቂ ቡድኑ ጽህፈት ቤት ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት፤ የመውጫ ቀነ ገደቡ ከተጠናቀቀ በኋላ ወታደራዊ ተቋራጮችን ጨምሮ የትኛውም የውጭ ኃይል መቆየት የለባቸውም ብለዋል።

"ከዶሃው ስምምነት በተቃራኒ ኃይላቸውን ወደኋላ ትተው የሚወጡ ከሆነ ቀጣይ እርምጃችን በአመራሩ የሚወሰን ይሆናል" ሲሉ ሻሂን ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ምላሽ እንሰጣለን፤ የመጨረሻው ውሳኔ የአመራራችን ይሆናል"ሲሉም አክለዋል፡፡

ዲፕሎማቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሌሎች የውጭ ሲቪሎች በታሊባን ኢላማ አይደረጉም ሲሉ አጥብቀው ገልፀው፤ ለእነሱ ቀጣይ የጥበቃ ኃይል አያስፈልግም ብለዋል፡፡

"እኛ የምንቃወመው የውጭ ወታደራዊ ኃይሎችን እንጂ ዲፕሎማቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሠራተኞቻቸው እንዲሁም በኤምባሲዎች የሚሠሩ ሰዎችን አይደለም። ይህም ሕዝባችን የሚፈልገው ነገር ነው፡፡ እኛ ለእነሱ ምንም ስጋት አንፈጥርም" ብለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በአፍጋኒስታን ትልቁ የአሜሪካ ወታደራዊ ካምፕ ከሆነው ከባግዳም አየር ጣቢያ የአሜሪካ ሠራዊት ለቆ መውጣቱን "ታሪካዊ ወቅት" በማለት ሻሂን ገልፀውታል፡፡

አሜሪካ እና የኔቶ አጋሮች ከታሊባን ጋር ባደረጉት ስምምነት መሠረት አልቃይዳ ወይም ሌላ አክራሪ ቡድን ታሊባን በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች እንዲንቀሳቀሱ ላለመፍቀድ ከተግባቡ በኋላ ነው ሁሉንም ወታደሮች ለማስወጣት ስምምነት ላይ የደረሱት፡፡

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአሜሪካ ወታደሮች ሙሉ በሙሉ መስከረም 9 ቀን እንዲወጡ ቀነ ገደብ ያስቀመጡ ሲሆን፤ ይህም የ9/11ዱ ጥቃት 20ኛ ዓመቱ የሚከበርበት እለት ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ሪፖርቶች ለቆ የመውጣት ሂደቱ በቀናት ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል እየጠቆሙ ይገኛሉ፡፡

የአፍጋኒስታንን መንግሥት ወክለው የተናገሩ አንድ የፓርላማ አባል በበኩላቸው የመውጣት ሂደቱ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

የፓርላማ አባሉ ራዝዋን ሙራድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት መንግሥት ለድርድር እና የተኩስ አቁም ዝግጁ መሆኑን እና ታሊባን ለሰላም ቁርጠኛ መሆኑንን ማረጋገጥ አለበት፡፡

ሻሂን ታጣቂ ቡድኑ በቅርቡ በተባባሱ ጥቃቶችና አመጽ ውስጥ ምንም ዓይነት ሚና አልተጫወተም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

የአፍጋኒስታን ወታደሮች ውጊያ በማቆማቸው ብዙ ወረዳዎች በሽምግልና በታሊባን እጅ መውደቃቸውን ተናግረዋል፡፡

ታጣቂዎቹ አሁን ላይ ወደ 400 የሚጠጉ ወረዳዎችን ወይም ከአገሪቱ አንድ አራተኛውን እንደተቆጣጠሩ ተናግረዋል፡፡

የታሊባን ቃል አቀባይ የአሁኑን መንግሥት "ሟች" ሲሉ የገለፁት ሲሆን፤ አገሪቱንም "እስላማዊ ኢሚሬትስ" ብለዋታል፡፡

ቡድኑ አገሪቱን ለማስተዳደር በአፍጋኒስታን መንግሥት የምርጫ ጥያቄዎችን የመቀበል እድሉ ሰፊ እንዳልሆነ አመላካች ነው ተብሏል፡፡

ሻሃን በታሊባንና በአፍጋኒስታን መንግሥት መካከል በተደረገው ድርድር እስካሁን የምርጫ ጉዳይ አልተነሳም ብለዋል፡፡