ምርጫው በሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ረገድ በብዙ መልኩ የተሳካ ነበር፡ ኢሰመኮ

ድምጽ የሚሰጡ ሴት

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ሰኞ በተደረገው ምርጫ ላይ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች የጎላ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳልታየና በሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ረገድ በብዙ መልኩ የተሳካ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እንደነበረ ገለጸ።

ኮሚሽኑ ምርጫ በተካሄደባቸው በተመረጡ አካባቢዎች ያሰማራው የክትትል ቡድን ያጠናቀረውን ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ እንዳመለከተው፤ በምርጫው መዳረሻ ቀናት እና በምርጫው ዕለት "በአብዛኛዎቹ ቦታዎች የጎላ ወይም የተስፋፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳልታየ" ጠቅሶ በምርጫው ሂደት የጎላ ችግር ሳያጋጥም በሰላም ተጀምሮ መጠናቀቁን ገልጿል።

ኢሰመኮ ጨምሮም በተወሰኑ አካባቢዎች በምርጫው ሂደት የተለያዩ ቀናት የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት፣ ተገቢ ያልሆነ እስር፣ በመራጮች ላይ የደረሰ ማስፈራራት፣ በምርጫ ታዛቢዎችና ጋዜጠኞች ላይ መጉላላትና ማዋከብ ማጋጠሙን አመልክቷል።

በተጨማሪም የምርጫው ሂደት ለአካል ጉዳተኛ ሰዎች ያለው አመቺነትና በተለያዩ ምክንያቶች በአገር ውስጥ ተፈናቅለው የሚገኙ ሰዎች የተሳትፎ መጠን ላይ በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።

ኮሚሽኑ ባጋጠሙ ሰብአዊ ጥሰት ድርጊቶች ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ ሰዎች ላይ በአፋጣኝ ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲኖር እንዲሁም በተለያዩ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ተሳትፎ ለማረጋገጥና አመቺ ለማድረግ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ባሉበት እና በተወሰኑ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫው ወደሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ በተደረገበት ሁኔታ ውስጥ ምርጫው መካሄዱን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ጨምሮም የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖች እራሳቸውን ከምርጫው ሂደት ባገለሉበት፣ ሌሎች የፖለቲካ ቡድን አመራሮች ደግሞ በቀረበባቸው የወንጀል ክስ ምክንያት በእስር ላይ በሚገኙበት ወቅት ምርጫው መካሄዱም ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ኮሚሽኑ አስታውሷል።

ቢሆንም ግን ኢሰመኮ ምርጫ በተካሄደባቸው ክልሎች በሚገኙ 99 የምርጫ ክልሎችና 404 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ የሚመለከታቸውን የምርጫ ባለድርሻዎችን በማነጋገርና የቀረቡለትን ጥቆማዎችንና አቤቱታዎችን በመመርመር ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት "የተወሰኑ የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ክፍተቶች የታዩ ቢሆንም፤ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች ላይ የጎላ ወይም የተስፋፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳልታየ" ገልጿል።

ኮሚሽኑ በሕግ የተሰጠውን የሰብአዊ መብቶች ክትትል የማድረግ ኃላፊነቱንና ተግባሩን በምርጫ ወቅትም እንዳይወጣ የሚያግዱ፣ የሚገድቡ ወይም የሚያሰናክሉ ሁኔታዎች በተለይም የምርጫ ጣቢዎችን ያለ እንቅፋት የመጎብኘትን በሚመለከት እንቅፋት እንዳይገጥመው የሚመለከታቸው አካላት እርምጃ እንዲወስዱና ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በምርጫው ሂደት የሰብአዊ መብቶች ጉዳይን ለመከታተል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ቢያርብም ኮሚሽኑ ይህንን ለማድረግ ከተፈቀደላቸው አካላት መካከል ባለመኖሩ ቦርዱ ሳይቀበለው ቀርቷል። ነገር ግን ኮሚሽኑ ክትትሉን ከምርጫ ጣቢያዎች ውጪ እንደሚያደረግ ማሳወቁ ይታወሳል።

ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች የተካሄደው ስድስተኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ የጎላ ችግር ሳያጋጥም በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ታዛቢዎች ባወጧቸው መግለጫዎች አመልክተዋል።