ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል የተባለው አዲስ ወደብ ተመረቀ

ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል የተባለውን አዲስ ወደብ እራሷን ነጻ አገር አድርጋ ባወጀችው ሶማሌላንድ በይፋ መርቃ ከፈተች።

ኮንቴይነሮችን የሚያስተናግደው አዲሱ ወደብ በአሁኑ ጊዜ በጂቡቲ በኩል አብዛኛውን የውጪና ገቢ ንግዷን የምታስተላልፈው የባሕር በር ለሌላት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተነግሯል።

ባለፈው ግንቦት ወር በዓለም ላይ ካሉ ግዙፍ የወደብ አስተዳዳሪ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የዱባዩ ዲፒ ዎርልድና የኢትዮጵያ መንግሥት በበርበራ ወደብና በኢትዮጵያ መካከል የንግድና የአቅርቦት መተላለፊያ ለመመስረት የ1 ቢሊየን ዶላር ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ሶማሌላንድ ያስገነባችው ይህ አዲስ ወደብ ሐሙስ ዕለት ተመርቆ ሲከፈት የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

ይህ ወደብ ሶማሌላንድ በአፍሪካ ቀንድ አገራትና በባሕረ ሰላጤው መካከል በሚኖረው የውጭ ንግድ ግንኙነት ላይ ቁልፍ ሚና እንዲኖራት ያስችላል ተብሏል።

የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የወደቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ በመጠናቀቁ የአገራቸው ህልም ዕውን መሆኑን በትዊተር ገጻቸው ላይ ገልጸው "አሁን በርበራ ወደብ የአካባቢው የንግድና የአቅርቦት ማዕከል ከመሆኑ ባሻገር ዓለም አቀፋዊ መዳረሻ ይሆናል" ብለዋል።

አዲሱ ወደብ በአሁኑ ወቅት አሉ የሚባሉ ግዙፍ የኮንቴይነር መርከቦችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን በዓመት ያስተናግድ የነበረውን 150,000 የኮንቴይነሮች ቁጥርን ወደ 500,000 ከፍ ያደርገዋል።

አሁን ከተመረቀው የወደቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ በተጨማሪ የማስፋፋት ሥራዎች በዲፒ ዎርልድ እንደሚከናወንና ቁጥራቸው በርካታ ግዙፍ የኮንቴይነር መርከቦችን እንዲያስተናግድና የሚቀበለውን የኮንቴይነሮችንም ቁጥር በዓመት ወደ ሁለት ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ እንደታቀደ ተነግሯል።

ሶማሌላንድ ከወደቡ ባሻገር የበርበራ ነጻ የንግድ ቀጠናንና መተላለፊያን በመገንባት ላይ ስትሆን በተለያዩ አገራት ድጋፍ እየተካሄዱ ያሉ ግዙፍ የመንገድ ግንባታዎች በዚህ ዓመት ይጠናቀቃሉ። ይህም በዋናነት በኢትዮጵያ በኩል ካለው መንገድ ጋር የሚገኛን ይሆናል ተብሏል።

ይህ ዘመናዊ መንገድ ከሶማሌላንድ ወደብ በኩል የሚመጣውን ጭነት በቀጥታ፣ በፍጥነትና በተቀላጠፈ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ የሚያደረግ በመሆኑ ለአገሪቱ አማራጭ መተላላፊያ ከመሆኑ በተጨማሪ የተቀላጠፈ አገልግሎትን እንድታገኝ ያደርጋል።

ወደቡን ማስፋፋት የሚያከናውነው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተቋም የሆነው ዲፒ ዎርልድ የበርበራ ወደብን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኘውን መንገድ ለማልማት ከኢትዮጵያ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር የተስማማ ሲሆን ይህም በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆን ተነግሯል።

ሶማሌላንድ በሶማሊያ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት ተካሂዶ የማዕከላዊው መንግሥት መውደቅን ተከትሎ እራሷን ነጻ አገር አድርጋ ያወጀች የሰሜን ሶማሊያ ክፍል ናት።

ሶማሌላንድ የእራሷ ጠንካራ መንግሥት ያላትና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያደረገች ግዛት ብትሆንም ከአፍሪካ ሕብረትም ሆነ ከሌሎች አገራት እውቅናን አላገኘችም።