ከሰላሳ በላይ ሴቶች ያለ እውቅናቸው ቪዲዮዋቸው በወሲብ ማሳያ ድረ-ገፅ ወጥቷል ሲሉ ከሰሱ

ፖርን ሃብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሰላሳ የሚበልጡ ሴቶች ታዋቂውን የወሲብ ድረ-ገፅ ፖርን ሃብ ከሰዋል። ክሱም ሳያውቁ ቪዲዮዋቸው በድረ-ገፁ ላይ ተጭኗል የሚል ነው።

ሴቶቹ እንደሚሉት ያለ ፈቃዳቸውና ያለ እውቀታቸው ቪዲዮዋቸው በድረ-ገፁ ላይ ተጭኗል በሚልም በካሊፎርኒያ ክስ ከፍተዋል።

ድረ -ገፁንም "የወንጀል ኢንተርፕራይዞችን" እየመራ ነው ሲሉ ወንጅለውታል።

ፖርን ሃብ በበኩሉ ይህ ፍፁም ውንጀላ ነው በማለት "ተቀባይነት የሌለው የማይረባ ክስና ፍፁም ሃሰት ነው" ሲል ክዷል።

ፖርን ሃብ በነፃ የሚታይ የወሲብ ድረ-ገፅ ቢሆንም ጥራት ያለው ቪዲዮዎችን እንዲሁ ሌሎች ተጨማሪ ይዘቶችን ለማየት ወርሃዊ ክፍያ ያስፈልገዋል።

በድረ ገፁ ያሉ ቪዲዮዎች በአብዛኛው በግለሰቦች የሚጫኑ ሲሆን ማንኛውም ሰውም ሊያያቸው የሚችሉ ናቸው። ነገር ኩባንያው እንደሚለው በድረ-ገፁ ላይ የሚጫኑ ማንኛውም ቪዲዮዎችን የሚቆጣጠሩ ሰዎች እንዳሉ ነው።

ፖርን ሃብ ለቢቢሲ እንደተናገረው "ፖርን ሃብ ህገ ወጥ የሆኑ ጉዳዮችን በምንም አይነት አይቀበልም። ምንም አይነት ቅሬታ ከመጣም ምርመራ እናካሂዳለን" ብሏል።

ድረ-ገፁ እንደሚለው ማንነታቸውን ግልፅ ያላደረጉ ተጠቃሚዎች ቪዲዮ ከጫኑ እንደሚያግድ ነው።

ነገር ግን የአሜሪካው ሚዲያና የቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ እንደሚለው ፖርን ሃብ በቪዲዮው ላይ ያሉ ሰዎች እድሜ ምን ያህል እንደሆነ አያረጋግጥም እንዲሁም በቪዲዮው ላይ ያሉት ግለሰቦች ፈቃድ መገኘቱንም አያረጋግጥም ብሏል።

ሴቶቹን ወክሎ እየተከራከረ ያለው ብራውን ሩድኒክ የተባለው ኩባንያ ክሱ ጥቃትን ለመከላከልና ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ህግ መስረት ያደረገ ነው ብሏል።

በክሱ ላይ ከተካተቱት ሴቶች መካከል አንደኛዋ ለሲቢኤስ እንደተናገረችው የወንድ ጓደኛዋ አስገድዶ ራቁቷን ቪዲዮ ሲያሰራት የ17 አመት ታዳጊ እንደነበረች ነው።

በኋላም ቪዲዮዋ ያለ እሷ እውቅና በድረ-ገፁ ላይ እንደወጣና ከጓደኛዋ እንደሰማች ተናግራለች።

ፖርን ሃብ የከሳሾቹንም ሁኔታ በቀላሉ እንደማያየውና እንደሚመረምርም አስታውቋል።

በታህሳስ ወር ኒውዮርክ ታይምስ በምርመራ ዘገባው ፖርን ሃብ በአብዛኛው የህፃናት ጥቃት፣ ከመደፈር ጋር የተያያዙ ቪዲዮዎች ተሞልቷል ቢልም ድረ-ገፁ ይህንን አይቀበልም።

ፖርን ሃብ ከሁለት አመት በፊት 42 ቢሊዮን ሰዎች ድረ-ገፁን የጎበኙ ሲሆን 6.83 ሚሊዮን ቪዲዮዎችም ተጭነዋል ብሏል።