ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምርጫ 2013፡ ከምርጫ ቀን በፊት ስላለው የጥሞና ጊዜ በጥቂቱ
በመጪው ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ብሔራዊ ምርጫ የምታካሂደው ኢትዮጵያ በትናንትና ዕለት የምረጡኝ ቅስቀሳ ተጠናቆ ቀጣዮቹ አራት ቀናት የጥሞና ወቅት መሆናቸውን አስታውቃለች።
በኢትዮጵያ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫ ከመደረጉ በፊት ያሉት አራት ቀናቶችም የጥሞና ወቅት እንደሆኑ ምርጫ ብሔራዊው የምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
በእነዚህም ቀናት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመገናኛ ብዙኃንና ሌሎች ተቋማት ሊያከናውኗቸው ስለሚገቡ ኃላፊነቶችም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዘርዝሯል።
በዚህም መሰረት የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎችና ደጋፊዎች ከድምፅ መስጫው ቀን ሰኔ 14 ከአራት ቀን በፊት የሚያካሂዱትን የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴዎችን ሊያቆሙ ይገባል ብሏል።
ቦርዱ ባወጣው መመሪያ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች በነዚህ አራት ቀናት ማንኛውም አይነት የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ አይችሉም።
ምርጫ ቦርዱ እንዳለው እነዚህ ቅስቀሳዎች በበይነ መረብ፣ በአካል፣ በአደባባይ፣ በአዳራሽ ስብሰባም ይሁን በማንኛውም መንገድ ምንም አይነት ቅስቀሳ ማድረግ አይቻልም ብሏል።
ቦርዱ መመሪያዎቹ ሊተገበሩ እንደሚገባ ባስታወቀበት በዚህ መግለጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ጉዳዮች ዙሪያ አስተያየት መስጠት አይችሉም፤ ቃለ መጠይቅ ማድረግ ክልክል ነው ብሏል።
ሚዲያዎችም ሊተገብሯቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉም በመግለጫው የተካተተ ሲሆን በዚህም መሰረት ምርጫ ተኮር እንቅስቃሴዎችን ማካሄድ አይችሉም ተብለዋል።
በነዚህ አራት ቀናት የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎችንም አግኝተው ቃለ መጠይቅ ማድረግ አይችሉም ብሏል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለምርጫው በተለያዩ መንገዶች ሲያደርጉ የቆዩትን የምርጫ ቅስቀሳዎች ረቡዕ ዕለት በተለያዩ ቦታዎች በማካሄድ ማጠናቀቃቸውን አሳውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ምርጫ ቦርድ በምርጫው ለሚሳተፉ የግል ተወዳዳሪ ዕጩዎች የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በማመኑ የ50 ሺህ ብር ድጋፍ ለመስጠት መወሰኑን ገልጿል።
በመላው አገሪቱ በዚህ ምርጫ በግላቸው ለመሳተፍ 148 ዕጩዎች እንደቀረቡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመልክቷል።
ስድስተኛ አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት ሲሆን በዚህ ቀን ምርጫ ማካሄድ ባልተቻለባቸው አካባቢዎች በተለዋጩ ቀን ጳጉሜ 1/ 2013ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።
በጳጉሜ 1 ድምፅ የሚሰጡ መራጮችም ቁጥር ወደ 38 ሚሊዮን ሊጠጋ እንደሚችልም ቦርዱ ገልጿል።
ከሶማሌና ሐረሪ ክልል በተጨማሪ በተለያዩ ክልሎች አንዳንድ ቦታዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ባለመጀመሩ ጳጉሜ 1 ምርጫ ይካሄዳል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ቦርዱ የለያቸው ቦታዎች ላይ ምርጫው የሚካሄደው ጳጉሜ 1 ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ለ54 የምርጫ ክልሎች በታተሙ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ የተለያዩ ጉድለቶች ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ የድምፅ መስጫ ወረቀት ጉድለት ካለባቸው መካከል በ27ቱ የምርጫ ክልሎች ጳጉሜ 1 ምርጫ እንዲካሄድ ተወስኗል።
ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተጨማሪ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ከምርጫው ጋር ሰኔ 14 በአንድ ቀን እንዲካሄድ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ሕዝበ ውሳኔው በሚካሄድበት ቦታ ያሉ የልዩ ወረዳ እና የዞን አመራሮች ለቦርዱ ቅሬታቸውን አቅርበው ነበር።
ከሦስት ቀናት በፊትም ቦርዱ ከአመራሮቹ ጋር ውይይት እንዳካሄደ ገልፆ የሕዝበ ውሳኔው ቀን ጳጉሜ 1 ፀንቶ እንደማይቀየር አስታውቋል።