የአፕል ሠራተኞች ወደ ቢሮ ተመልሶ የመሥራት ሐሳብን እየተቃወሙ ነው

ቲም ኩክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአፕል ሠራተኞች ለሥራ ወደ ቢሮ ተመለሱ የሚለውን ሐሳብ እየተቃወሙ ነው።

የአፕል አለቃ ቲም ኩክ ሠራተኞች ከመስከረም ጀምሮ ቢያንስ በሳምንት ሦስት ቀን ቢሮ መግባት እንዳለባቸው ተናግሯል።

ይህንን ውሳኔ ባለፈው ሳምንት ካስታወቀ ወዲህ ሠራተኞች ተቃውሞ እያሰሙ ይገኛሉ።

ምቹ የሥራ ሰዓት እንዲኖር የሚጠይቅ የሠራተኞች ደብዳቤ እጁ እንደገባ 'ዘ ቨርጅ' ዘግቧል።

ደብዳቤ ላይ "የአፕል ፖሊሲ አንዳንድ ሠራተኞች ሥራውን ለቀው እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል" ተብሏል።

ለሠራተኞች የሚመች ሰዓት ካልተመደበ፤ ተቀጣሪዎቹ ከቤተሰሰብ ሕይወት፣ ከጤናቸው እና ከሥራቸው እንዲመርጡ እንደሚገደዱም በደብዳቤው ተመልክቷል።

"በተለይ ባለፈው ዓመት የምንናገረው ነገር ሰሚ እንዳላገኘ ብቻ ሳይሆን ሆነ ተብሎ ችላ እንደተባልን ይሰማናል" ሲሉ ሠራተኞቹ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

የሥራ ሰዓትን ለተቀጣሪዎች ምቹ በማድረግ ረገድ የአፕል አለቆች ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንዳልሆነም ይከሳሉ።

ዘ ቨርጅ እንደዘገበው፤ ሠራተኞቹ ደብዳቤውን የጻፉት ፊርማ ለማሰባሰብ ነው።

ቲም ኩክ ለአፕል ሠራተኞች በጻፈው ማስታወሻ "ከሰዎች ጋር መሥራት እና የመሥሪያ ቤት ግርግር ናፍቆኛል" ብሏል።

ሠራተኞች በሳምንት ሦስት ቀን ቢሮ እንዲገቡ ከሚለው መመሪያ በተጨማሪ የአንዳንድ ክፍል ተቀጣሪዎች በሳምንት አራት ወይም አምስት ቀን ይግቡ የሚልም ተጠቅሷል።

የአፕል ሠራተኞች በጻፉት ደብዳቤ፤ ወደ ቢሮ የመመለስ ውሳኔ በእያንዳንዱ ክፍል ውይይት እንዲወሰን ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በድርጅቱ ውስጥ ጉዳዩን የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት እንዲካሄድ እና ሠራተኞች ከቤት ወይም ከቢሮ ሲሠሩ የሚገጥማቸውን ከግምት ያስገባ ውሳኔ እንዲተላለፍ ጠይቀዋል።

ከቢሮ ውጪ መሥራት ምን አይነት ውጤት አለው? የሚለውን ከቢሮ ቆይታ ጋር እንዲነጻጸርም ሠራተኞቹ ጠይቀዋል።

አያይዘውም የአፕል ሠራተኞች ሥራ ሲለቁ፤ የመልቀቂያ ምክንያታቸው ከቢሮ ቆይታ ጋር ስለመሆኑ ድርጅቱ እንዲያጣራ አሳስበዋል።

ጉግል ሠራተኞቹ ከመስከረም ጀምሮ በሳምንት ሦስት ቀን ቢሮ እንዲገቡ ወስኗል።

ሌሎች የቴክኖሎጂ ተቋሞች ግን ሠራተኞች ወደ ቢሮ እንዲመለሱ ጫና አላሳደሩም።

ፌስቡክ ከቢሮ ውጪ ሆኖ መሥራት "የወደፊት አቅጣጫችን ነው" ብሏል። ትዊተር በበኩሉ ሠራተኞቹን "እስከመጨረሻው ድረስ ከቤት ሥሩ" ብሏቸዋል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በመላው ዓለም ብዙ መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸው ከቤት እንዲሠሩ ፈቅደዋል።