ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና ዜጎቿ እስከ ሦስት ልጆች መውለድ እንዲችሉ ፈቀደች
ጥንዶች በሚወልዷቸው ልጆች ቁጥር ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ስታደርግ የቆየችው ቻይና ዜጎቿ እስከ ሦስት ልጆች ድረስ መውለድ እንዲችሉ ፈቀደች።
ውሳኔው የተላለፈው በአገሪቱ የሕዝብ ቆጠራ ሲደረግ የወሊድ መጠን መቀነሱ ከታወቀ በኋላ ነው።
ቻይና አንድ ልጅ ብቻ መውለድ የሚፈቅደውን ፖሊሲ የሰረዘችው እአአ በ2016 ነበር። ጥንዶች ሁለት ልጆች እንዲወለዱ ከፈቀደች በኋላም ግን የወሊድ ቁጥር አላደገም።
በቻይና ከተሞች ልጆችን ለማሳደግ የሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ ብዙ ጥንዶች እንዳይወልዱ አድርጓል።
እስከ ሦስት ልጆች ድረስ እንዲወለድ ፕሬዘዳንት ዢ ዢፒንግ መፍቀዳቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የዢንዋ ዘገባ እንደሚያሳየው፤ የአገሪቱን የሕዝብ ቁጥር ከመጨመር ባሻገር የእድሜ ባለጸጎችን ለመንከባከብ እቅድ ይነደፋል።
የፖሊሲ ለውጡ ምን ያህል ለውጥ ያመጣል? ሲሉ ከጠየቁ ተንታኞች አንዱ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ሃዎ ዘሁ ነው። "የልጅ ቁጥርን የመጨመር ፖሊሲ ውጤታማ ቢሆን ኖሮ ሁለት ልጆች እንዲወለዱ ሲፈቀድ ለውጥ ይታይ ነበር" ብሏል።
ጥንዶች ከሁለት ልጆች በላይ መውለድ እንደማይፈልጉና ምክንያቱም የኑሮ ውድነት እንደሆነ አስረድቷል።
ሁለት ልጆች መውለድ ሲፈቀድ ነገሮች ካልተለወጡ አሁን ምን አዲስ ነገር ይፈጠራል? ብለው የሚጠይቁ ብዙ ናቸው።
ለዘመናት ቻይናውያን ያለ እህት ወይም ወንድም መኖርን ስለለመዱ ትንሽ ቁጥር ያለው ቤተሰብ አያሳስባቸውም።
በርካታ ጥንዶች ብዙ ልጆች ከመውለድ ይልቅ አንድ ልጅ ወልዶ የሚያስፈልገውን ነገር በአጠቃላይ አሟልቶ በማሳደግ ያምናሉ።
በዚህ ወር የወጣው የቻይና ሕዝብ ቆጠራ የሚያሳየው አምና 12 ሚሊዮን ልጆች እንደተወለዱ ነው።
2016 ላይ የተወለዱት 18 ሚሊዮን ልጆች ሲሆኑ፤ ዝቅተኛ የልጆች ቁጥር የተመዘገበው በ1960ዎቹ ነበር።
በርካታ የቻይና መገናኛ ብዙሃን ሦስት ልጆች መውለድ መፈቀዱን መነጋገሪያ አድርገውታል። በቻይና ማኅበራዊ ሚዲያ ዌቦ ላይም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አስተያየት እየሰጡበት ነው።
አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ቻይናውያን ጥንዶች ብዙ ጫና ስላለባቸው ተጨማሪ ልጆች የመውለድ እቅድ የላቸውም።
ጥንዶች ሲወልዱ ከሥራ ቦታቸው ተገቢው ማበረታቻ እንደሌለ አጣቅሰዋል። ዘለግ ላለ ሰዓት የሚሠሩ፣ ከአንድ በላይ ሥራ የሚይዙ ወይም የተለያየ ትምህርት የሚማሩም መኖራቸው እንደ ምክንያት ተነስተዋል።
ቻይና ሁለት ልጆች መውለድ ስትፈቅድ ለተወሰነ ጊዜ የወሊድ መጠን ቢጨምርም እንዳልዘለቀ የኢኮኖሚስት ዋና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዩ ሱ ይናገራሉ።
እአአ በ1979 አንድ ልጅ ብቻ የውለድ ፖሊሲ ከወጣ በኋላ የቻይና ቤተሰብ መዋቅር የተቀረጸው በዚህ መርህ ነው።
ከአንድ በላይ ልጅ የወለዱ ጥንዶች ከሥራ መባረር፣ ጽንስ እንዲያቋርጡ መገደድ እናም ሌላ ቅጣት ደርሶባቸዋል።
የአንድ ልጅ ፖሊሲ ትዳር ላይም ጫና አሳድሯል። በተለምዶ ለወንድ በሚያደላው የቻይና ማኅበረሰብ ወንዶች የተሻለ ማኅበራዊና የምጣኔ ሀብት ደረጃ እንዲኖራቸውም አድርጓል።
በሌላ በኩል አዲሱ ፖሊሲ የከተማና የገጠር የኑሮ ሁኔታን እንደሚለውጥ የሚገምቱ ተንታኞች አሉ። እንደ ቤጂንግ ባሉ ከተሞች የሚኖሩ ሴቶች ልጅ ሳይወልዱ ሲቆዩ ከከተማ ውጪ ያሉት ግን ሰፊ ቤተሰብ የመመስረት ፍላጎት እንደሚኖራቸው ይገመታል።
በዊስኮንሰን ማዲሰን ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ዶ/ር ይ ፉሺን እንደሚሉት፤ ብዙ ኢንዱስትሪዎች ቻይና ተኮር እየሆኑ በመምጣታቸው የቻይና የሕዝብ ቁጥር መቀነስ አሳሳቢ ይሆናል።