ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኬንያ ፖለቲከኞች ሕገ-መንግሥቱን ለማሻሻል ያደረጉት ጥረት በፍርድ ቤት ታገደ
የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በገዢው መንግሥት ድጋፍ ያገኘውን የሕገ-መንግሥት ማሻሻል ሐሳብ ውድቅ አድርጎታል።
ፍርድ ቤቱ የወሰነው ውሳኔ በፈረንጆቹ 2017 ኡሁሩ ኬንያታ ምርጫውን አላሸነፉም ብሎ ፍርድ ቤት ከሰጠው ፍርድ በኋላ ትልቁ ነው ተብሏል።
ዳኛው በተለምዶ ቢቢአይ እየተባለ የሚጠራው የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ዕቅድ ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም ሲሉ ብይናቸው ሰጥተዋል።
ዳኛው አክለው ማሻሻያው ሕገ ወጥና ቅርፅ አልባ ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ዋነኛ ተቀናቃኛቸው የነበሩት የአሁኑ ጓደቸው ራይላ ኦዲንጋ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያው እውን እንዲሆን ደፋ ቀና ሲሉ ነበር የከረሙት።
ሁለቱ መሪዎች ማሻሻያው ሕግ አውጪው የመንግሥት ክንፍ እንዲስፋፋና የሃገሪቱ ፖለቲካ የበለጠ አሳታፊ እንዲሆን ያስችላል ሲሉ ይሞግታሉ።
ነገር ግን ተቺዎች ማሻሻያው የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በርስ ለመጠቃቀም ያመቻመቹት ነው ሲሉ ይከራከራሉ።
ነቃፊዎቹ አክለው ማሻሻያው የሕዝብ እንደራሴዎች ቁጥርን ከፍ ያደርገዋል፤ ይህ ደግሞ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቃ ለምትገኘው ኬንያ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው ይላሉ።
ቢቢአይ በተሰኘ ቅፅል ስሙ የሚታወቀው የማሻሻያ ሐሳብ ወደ ብሔራዊው ሸንጎና ሴኔት ተልኮ በአብላጫ ድምፅ አልፎ ነበር።
ነገር ግን ወደ ፕሬዝደንቱ ጠረጴዛ ተልኮ የመጨረሻው ፊርማ ከማረፉ በፊት ነው ሐሙስ ዕለት በፍርድ ቤት የታገደው።
ማሻሻያው ፀደቀ ማለት ኬንያዊያን በሚቀጥለው ዓመት ከሚደረገው ምርጫ በፊት ለሕዝበ ውሳኔ ድምፃቸውን ይሰጣሉ ማለት ነው።
ዳኞች ምን አሉ?
ለአራት ሰዓታት በቴሌቪዥን መስኮት ቀጥታ በተላለፈው ችሎት ዳኞቹ ፕሬዝደንት ኬንያታ የሃገሪቱን ሕገ-መንግሥት ጥሰዋል ብለዋል።
አክለው ኡሁሩ የመሠረቱት የቢቢአይ ኮሚቴ ሕገ-ወጥ ነው፤ ፕሬዝደንቱ የተሰጣቸውን የመሪነት ሚና በአግባቡ አልተወጡም ብለዋል።
ዳኞቹ፤ ፕሬዝደንቱን በግላቸው ሊከሷቸው እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
ፖለቲከኞቹ ማሻሻያውን ለማፅደቅ በሚል የሰበሰቡት 5 ሚሊዮን ድምፅ ይህንን ሐሳብ የዜጎች አያደርገውምም ብለዋል ዳኞቹ።
የፍርደ ቤቱ ውሳኔ ፕሬዝደንቱን ከሥልጣናቸው ሊያስነሳቸው የሚችል ቢሆንም ነገር ግን የማሻሻያውን ሐሳብ በአብለጫ ድምፅ ያሳለፈው ፓርላማ ይሄን ያደርጋል ተብሎ አይጠበቅም።
ቢቢአይ፤ ኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲኖራት፤ ቢያንስ 70 አውራጃዎችና 300 ተጨማሪ የፓርላማ መቀመጫዎች እንዲጨመሩ ሐሳብ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱ የማሻሻያ ሐሳቡን ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ መንግሥት ይግባኝ ይጠይቃል ተብሎ ቢጠበቅም ሕግ አዋቂዎች ግን ውጤቱ ከዚህ የተሻለ ይሆናል ብለው አያምኑም።