በእስራኤልና ፍልስጥኤም የተነሳው ግጭት ከፍ ወዳለ ጦርነት እንዳያመራ ተፈርቷል

የእስራኤል መኪና ሲቃጠል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በእስራኤል ሰራዊትና በፍልስጥኤም ታጣቂዎች መካከል በጋዛ ሰርጥ የተነሳው ግጭት በከፍተኛ ሁኔታ ተጋግሎ ወደ ጦርነት እንዳያመራ መፈራቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

አንድ ሺህ የሚገመቱ ሮኬቶች በፍልስጥኤም ታጣቂዎች መወንጨፈቻውን እስራኤል አስታውቃለች። እነዚህ ሮኬቶች በ38 ሰዓታት ሲሆን አብዛኛዎቹ ደግሞ ኢላማ ያደረጉት ቴልአቪቭን ነው።

እስራኤል በበኩሏ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአየር ጥቃቶችን ማክሰኞና ረቡዕ የፈፀመች ሲሆን በጋዛ የሚገኙ ሁለት የመኖሪያ ህንፃዎችን ሙሉ በሙሉ አውድማለች።

በያዝነው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ 43 ፍልስጥኤማውያንና ስድስት እስራኤላውያን ተገድለዋል።

ከነዚህም መካከል 13 ፍልስጥኤማውያን ህፃናት ይገኙበታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እንዳሉት ግጭቱ ከፍተኛ ስጋትን እንዳሳደረባቸው ነው።

በአሁኑ ወቅት የጋዛ ጎዳናዎች በህንፃ ፍርስራሾች ተሞልተዋል። በእስራኤል አየር ጥቃቶች ምክንያት ህንፃዎች ወድመዋል፣ መኪኖች ተቃጥለዋል።

አረብ እስራኤላውያን በተለያዩ የእስራኤል ከተሞች በቁጣ የተሞሉ ተቃውሞችን አድርገዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በቴልአቪቭ አቅራቢያ የምትገኘው ሎድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጥሎባታል።

በሎድ ከተማ በተነሳው አመፅ መኪኖች ጋይተዋል እንዲሁም 12 ሰዎች ተጎድታል። የከተማው ከንቲባም ስማቸው ከእርስ በእርስ ጦርነት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ይገኛል።

ለሳምንታት ያህል በእስራኤል ፖሊስና በፍልስጥኤማውያን ሰልፈኞች መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ ወደ ግጭት አምርቷል። በእስልምናና በአይሁድ እምነት ተከታዮች ዘንድ ቅድስት ተብላ የምትጠራው ስፍራ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ መጋጋል ተፈጥሮ ነበር።

ከአውሮፓውያኑ 2014 በኋላ በሁለቱ ኃይሎቸ መካከል የተፈጠረ ከፍተኛ ግጭት መሆኑንም እስራኤል አስታውቃለች።

ከጋዛ ከተወነጨፉት 1 ሺህ 50 ሮኬቶችና ከባድ መሳሪያዎች መካከል 850ዎቹ በእስራኤል እንዳረፉና ሌሎች ደግሞ በሮኬት መቃወሚያ አማካኝነት ተመልሰው ወደ ጋዛ እንዳረፉ የእስራኤል ጦር አስታውቋል።