ማንቸስተር ሲቲ ፒኤስጂን በመርታት የቻምፒዬንስ ሊግ ጉዞውን ቀጥሏል

ማንቸስተር ሲቲ በቻምፒየንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ ፓሪስ ሴይንት ዠርሜይንን በመርታት ወደ ፍፃሜው የሚያደርገውን ጉዞ አመቻችቷል።

የፔፕ ጉዋርዲዮላ ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ ተወስደቦት የነበረውን ብልጫ በሁለተኛው አጋማሽ በመቀልበስ ነው ድል መምታት የቻለው።

የፒኤስጂው ማርኪንሆስ ከዲ ማርያ የተሻማለትን ኳስ በጭንቅላቱ ወደ ጎል ቀይሮ የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ አንድ ለምንም ነበር የተጠናቀቀው።

የፈረንሳዩን ክለብ መዳከም ያዩት ሲቲዎች በሁለተኛው አጋማሽ በሙሉ ኃይላቸው ነበር ሲያጠቁ የነበሩት።

ኔይማርና ምባፔ በመጀመሪያው አጋማሽ ያሳዩትን ብቃት መድገም ባቃታቸው ወቅት ነው የሲቲ ኬቪን ደ ብራይን ያሻማት ኳስ ሁሉንም ዘልቃ መረብ ላይ ያረፈችው።

ከሰባት ደቂቃ በኋላ አልጄሪያዊው ሪያድ ማህሬዝ ያገኘውን የቅጣት ምት ዕድል በግራ እግሩ አሹሩ ከመረብ መዶል ችሏል።

ይህ አልበቃ ያለው ፈረንሳዊው ቡድን ፒኤስጂ የቀድሞው የኤቨርተኑ አማካይ ኢድሪሳ ጉዬ በቀይ ተሰናብቶበት አማራጩ መከላከል ሆኖ አምሽቷል።

ሲቲዎች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ለቻምፒዬንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ መድረስ የቻሉት።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ መሪዎቹ ሲቲዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በጣም ድንቅ ብቃት እያሳዩ የነበሩት ፒኤስጂዎችን በመበለጥ የቻምፒዬንስ ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።

የፒኤስጂዎቹ ኔይማርና አንኸል ዲ ማሪያ የመጀመሪያውን 45 ደቂቃ የሲቲን ተከላካይ ሲያስጨንቁ ቢያመሹም ይህን በሁለተኛው 45 መድገም አልቻሉም።

"ከምባፔ፣ ኔይማርና ዲ ማሪያ ጋር መፋለም ቀላል ባይሆንም የመጀመሪያውን አጋማሽ ውጤት ቀልብሰናል" ብለዋል የሲቲው አሠልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ።

"ባሳየነው ብቃት ተደስቻለሁ። ነገር ግን ይህ የመጀመሪያው ጨዋታ ነው። ብዙ ይቀረናል።"

ቡድናቸው በሁለተኛው አጋማሽ ደካማ ብቃት ማሳየቱን ያመኑት የፒኤስጂው ፖቼቲንሆ በሁለተኛው ጨዋታው ውጤቱን ለመቀልበስ እንደሚጫወቱ ተናግረዋል።

የጉዋርዲዮላ ሲቲ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቻምፒዬንስ ሊጉ ያስመዘገበው ታሪክ በታክቲክ ስህተቶች የተሞላ ነው። ዘንድሮ ግን ነገሮች እየሰመሩ ይመስላሉ።

በቀጣዩ ሳምንት የመልስ ጨዋታ በሜዳቸው ፒኤስጂን የሚያስተናግዱት ሲቲዎች አዲስ ታሪክ ከመፃፍ የሚያግዳቸው ያለ አይመስልም።

ነገር ግን የመጀመሪያ የቻምፒዬንስ ሊግ ዋንጫቸው ለማንሳት ትግል እያደረጉ ያሉት ፒኤስጂዎች ሁለተኛውን ጨዋታ ለሲቲ ቀላል ያደርጉታል ተብሎ አይታሰብም።

የሁለቱ ቡድን አሸናፊ ከቼልሲና ማድሪድ አሸናፊ ጋር ለመፍፃሜ የሚፋለም ይሆናል።

ቼልሲና ሪያል በማድሪድ ሜዳ ተፋልመው አንድ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል። የመልሱ ጨዋታ ቀጣይ ሳምንት ረቡዕ በቼልሲ ሜዳ ይካሄዳል።

የፍፃሜው ጨዋታው ግንቦት 21 በቱርኳ ኢስታንቡል ይከናወናል።