ደቡብ ሱዳን ወደለየለት ጦርነት ልትገባ እንደምትችል የተባበሩት መንግሥታት አስጠነቀቀ

በፕሬዝደንት ሳልቫ ኪርና

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በፕሬዝደንት ሳልቫ ኪርና

የተባበሩት መንግሥታት ደቡብ ሱዳን ወደ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እያደረገች ያለው ጉዞ ቀርፋፋ መሆኑ ከፍ ወዳለ ግጭት ሊያመራ ይችላል ሲል ስጋቱን ገለጸ።

ድርጅቱ እንዳለው ደቡብ ሱዳን ወደ ሰላማዊ መንገድ መምጣት ካልቻለች ወደ ቀድሞው ዓይነት ግጭት ልትመለስ ትችላለች።

አንድ አዲስ የወጣ ሪፖርት እንደሚያሳየው የጦር መሣሪያ ዝውውር ማዕቀብ እንዲጣልና የሰላም ሂደቱን የሚያደናቅፉ ሰዎች እንዲቀጡ ሐሳብ አለ።

የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት የተፈረመው ከሦስት ዓመት በፊት ነበር።

ነገር ግን ከዚህ ስምምነት በኋላ በፕሬዝደንት ሳልቫ ኪርና በተቀናቃኛቸው ሪዬክ ማቻር ደጋፊዎች መካከል በርካታ ግጭቶች ተካሂደዋል።

ከሰላም ስምምነት በፊት የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩት ሪዬክ ማቻር ከስምምነቱ በኋላ ይህን ሥልጣናቸውን መልሰው ማግኘታቸው አይዘነጋም።

ነገር ግን ደጋፊዎቻቸው አሁንም ከሳልቫ ኪር ኃይሎች ጋር መፋለማቸውን እንደቀጠሉ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት እንደሚያሳየው ይህ ግጭት ሰብዓዊ እርዳታዎች በሰላም እንዳይደርሱ እያደናቀፈ ነው።

በሁለቱ ኃይሎች መካከል በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ በርካታ ደቡብ ሱዳናውያን እርዳታ ጠባቂ ለመሆን ተገደዋል።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ደቡብ ሱዳን ላይ ተጥሎ የሚገኘው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ለአንድ ዓመት እንዲራዘመ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።

የአሜሪካ መንግሥት በተመረጡ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ባለስልጣናት ላይ ማዕቀቦችን ጥሎ ይገኛል። ማዕቀብ ከተጣለባቸው መካከል የቀድሞ ምክትል ፕሬዝደንት ታባን ዴንግ ጋይ ይገኙበታል።

የቀድሞው ፕሬዝደንት ንብረቶቻቸውን እንዳያንቀሳቅሱ በአሜሪካ እግድ ተጥሎባቸዋል።

ደቡብ ሱዳን ከየት ወዴት?

ስምምነቱ ስድስት ዓመት የዘለቀውንና ከ400 ሺህ በላይ ሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈው እንዲሁም ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያፈናቀለውን የደቡብ ሱዳናውያን የእርስ በእርስ ጦርነት ያስቆማል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

ደቡብ ሱዳን ረዥም ዓመት ከወሰደው ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ከሱዳን ተለይታ ራሷን የቻለች አገር የሆነችው እኤአ በ2011 ነው።

ፕሬዝዳንት ኪር ምክትል ፕሬዝዳንታቸው የነበሩትን ማቻርን ከስልጣናቸው ካነሱ በኋላ ደቡብ ሱዳን በወርሃ ታኅሣሥ 2013 ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ገብታለች።

በወቅቱ ፕሬዝዳንት ኪር፣ ማቻር መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ እያሴሩ ነው ብለው የወነጀሏቸው ቢሆንም ማቻር ግን አስተባብለዋል።

በደቡብ ሱዳን የተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ፖለቲካዊ አለመግባባት የፈጠረው ቢሆንም የጎሳና የኃይል ክፍፍል መልክም አለው።

የደቡብ ሱዳን ሁለት ትልልቅ ጎሳዎች ዲንካና ኑዌር ሁለቱ የፖለቲካ አመራሮች የተገኙባቸው ሲሆን አንዳቸው ሌላኛቸውን ወገን ማጥቃታቸውን በመጥቀስ ይወነጃጀላሉ።