የጣልያን ፖሊስ 30 ተጠርጣሪ የናይጄሪያ 'ወሮበላ' ቡድን አባላትን ያዘ

ተጠርጣሪዎቹ በሰዎችና በዕፅ ዝውውር፣ በወሲብ ንግድና በኢንተርኔት የሚደረግ ውንብድና ላይ በመሳተፍ የሚሉትን ጨምሮ ከ100 በላይ ክስ እንደሚጠብቃቸው ፖሊስ ገልጿል።

የጣልያን ፖሊስ በመላው አገሪቱ አሰሳ ካካሄደ በኋላ የናይጄሪያ 'ብላክ አክስ' የማፊያ ብድን አባላት እንደሆኑ የተጠረጠሩ 30 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አዋለ።

ተጠርጣሪዎቹ በሰዎችና በዕፅ ዝውውር፣ በወሲብ ንግድና በኢንተርኔት የሚደረግ ውንብድና ላይ በመሳተፍ የሚሉትን ጨምሮ ከ100 በላይ ክስ እንደሚጠብቃቸው ፖሊስ ገልጿል።

የወንበዴ ቡድኑ 'ዳርክ ዌብ' በተሰኘ ድብቅ የኢንተርኔት መረብ ውስጥ በዲጂታል ገንዘብ ወይም ቢትኮይን በመገበያየትም ተጠርጥሯል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ970ዎቹ በናይጄሪያ ብቅ ያለው 'ብላክ አክስ' በመድፈር፣ በአካል ማጉደልና በመግደል ይታወቃል።

ቡድኑ ቀስ በቀስ ጠንካራ የግንኙነት መረቡን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ማሳደግ ችሏል።

በጣልያን የሚገኘው ቡድን ናይጄሪያ ካለው በአርማ፣ በቃላት አጠቃቀምና ተግባሮቻቸውን በማየት ቀጥታ ግንኙነት እንዳላቸው ፖሊስ ገልጿል።

በጣልያን በሚገኙ 14 አውራጃዎች በተደረገ አሰሳ ነው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል በጣሊያን 'የብላክ አክስ' መሪ ነው የተባለ የ35 ዓመት ግለሰብም ይገኝበታል።

"ይህ የፖሊስና የፍትሕ አካላት ተግባር ወንጀላቸውን ማስፋፋት ለሚፈልጉ አዳዲስና የቀድሞ የወንበዴ ቡድኖችን ለማደን ያለውን አቅም የሚረጋግጥ ነው" ሲሉ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሉቺያና ለሞራጋሴ ባወጡት መግለጫ አስረድተዋል።

'ብላክ አክስ' ማነው?

በናይጄሪያ የተመሠረተው ቡድኑ በዓለም ላይ ዝነኛ ስም ያለው በድብቅ የሚንቀሳቀስ የወንበዴዎች ስብስብ ነው።

'ብላክ አክስ' ከ50 ዓመታት በፊት የተመሠረተና ቀድሞ 'ኒዎ ብላክ ሙቭመንት' በሚል የሚታወቅ ሲሆን፤ ዓላማዬ የሚለው ደግሞ ጥቁር ዘርን "ነፃ ማውጣት" የሚል ነበር።

ሆኖም ቡድኑ ዓላማዬ ብሎ ከያዘው በተቃራኒ ሰዎችን መግደልና መድፈር መታወቂያው ሆነ።

ከሚሊሻ ጋር የሚመሳሰል የዕዝ ሰንሰለት ያለውም ነው።

ይህ የ'ወሮበላ' ቡድን በናይጄሪያ በመቶች የሚቆጠሩ አባላቱ ቢታሰሩበትም አሁንም አዳዲስ አባላትን በተለይም ከዩኒቨርስቲ እንደሚመለምል ተዘግቧል።