ሶማሊያ ውስጥ ሚሊዮኖች ለረሃብ መጋለጣቸው ተነገረ

ደረቅ የአየር ሁኔታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዚህ ዓመት ሶማሊያን ባጋጠሟት ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝቧ የሚያስፈልገውን ምግብ ሊያገኝ እንደማይችል ተነገረ።

ሴቭ ዘ ችልድረን የተባለው ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት እንዳለው የበረሃ አንበጣ ወረራ፣ የአየር ፀባይ ለውጥ እንዲሁም ከሚያስፈልገው አማካይ የዝናብ መጠን በታች መዝነብ በርካታ ሕዝብን ለችግር አጋልጦታል።

በዚህም ሳቢያ በሶማሊያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን በቂ የምግብ ምርት እንደማያገኙ አመልክቷል።

ሴቭ ዘ ችልድረን እንዳለው በዚህ ሳቢያም በምርት ወቅቱ በሶማሊያ ውስጥ የሚመረተው የሰብልና የአትክልት ምርት በ80 በመቶ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም የሶማሊያ ዋነኛ ኢኮኖሚያዊ ገቢ ምንጭ የሆነው የቀንድ ከብት ሽያጭም በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳ ተነግሯል። በዚህም ሳቢያ ሶማሊያ ለሽያጭ የምታቀርባቸው የቁም እንስሳት ገቢም በ55 በመቶ ያሽቆለቁላል ተብሎ ተሰግቷል።

ግብረ ሰናይ ድርጅቱ እንዳመለከተው በተከሰተው የምግብ እጥረት ምክንያት እናቶች ለልጆቻቸው በቀን አንድ ጊዜ ምግብ ለማቅረብ ተስፋ በሚያስቆረጥ ሁኔታ እየተቸገሩ ነው።

በዚህም ሳቢያ አንዳንድ ህጻናት ከአሁኑ ተገቢውን ምግብ ባለማግኘታቸው ሳቢያ በጤናቸው ላይ ጉዳት እየታየ ነው።

በተለያዩ ተፈጥሯዊ ክስተቶች ሳቢያ ለምግብ እጥረት የተጋለጡት ሶማሊያውያን ሁኔታ ቀስ በቀስ ወደ አደገኛ ሁኔታ እንዳይሄድ ስጋት ተፈጥሯል።

ለዚህ ዓመት የተቀመጡት ግምቶች እንዳመለከቱት በደቡባዊ ሶማሊያ የሚኖሩ ድሃ ቤተሰቦች ከሚያመርቱት ውስጥ ለምግብነት ሊያገኙ የሚችሉት ምርት 15 በመቶ ብቻ እንደሚሆን ተነግሯል።

ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ አስቸጋሪ ሁኔታ በሚገጥማቸው ጊዜ ከምርታቸው ግማሽ ያህሉን አግኝተው የምግብ እጥረቱን ጊዜ ለማለፍ ይችሉ የነበረ ሲሆን የአሁኑ ግን የከፋ ነው ተብሏል።

ሶማሊያ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የቆየች ሲሆን ይህም በመሰረተ ልማቶቿ ላይ ከባድ ውድመትን በማስከተሉ ተፈጥሯዊ ችግሮች ከሚያስከትሉት ጉዳት ጋር ተዳምሮ ሕዝቡ ላይ ከባድ ጫናን አስከትሏል።

በተጨማሪም አልሻባብ የተባለው ታጣቂው ጽንፈኛ ቡድንም አገሪቱ ወደ መረጋጋት እንዳትመለስ ምክንያት ከመሆኑ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጽማቸው የሽብር ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ይገደላሉ።

በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ሕብረት የሚደገፈው የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥትም በውስጥ በተደጋጋሚ በሚያጋጥመው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሳቢያ በውጥረት ውስጥ በመሆኑ የታጣቂ ቡድኑንና ተፈጥሯዊ ክስተቶችን በመቆጣጠር አገሪቱን ለማረጋጋት ፈተና ገጥሞት ቆይቷል።