የከተሜውን ህይወት የከተማ ግብርና ያቀለዋል የሚሉት አቶ እስክንድር

አቶ እስክንድር ሙሉጌታ በአዲስ አበባ በሚገኙ አስር የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተለያዩ ችግኞችን በማዘጋጀት ለሽያጭ ያቀርባሉ።

በተጨማሪም በእነዚህ አስር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድንች፣ ሽንኩርት እና ቲማቲም በማልማት በትምህርት ቤቶቹ ለሚካሄደው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በሽያጭ እያቀረቡ ገቢ እንደሚያገኙ ይገልፃሉ።

አቶ እስክንድር ከሚሰሩባቸው አስሩ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል መጋቢት 28 ፣ መቅደላ፣ ደምቦስኮ፣ ብሩህ ተስፋ፣ ቆጣሪ፣ ስብስቴ፣ አቡነ ባስሊዎስ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

አቶ እስክንድር ሥራቸውን የጀመሩባቸው ሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም የሚሰጡ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በአገር አቀፍ ደረጃ 1.5 ሚሊዮን ተማሪዎች በምገባ ፕሮግራም ውስጥ መታቀፋቸውን የሚናገሩት አቶ እስክንድር በአዲስ አበባ ደግሞ 300 ሺህ ተማሪዎች በዚሁ መረሃ ግብር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

ይህንን የምገባ ፕሮግራም ለመሸፈን የሚያስፈልገው ገንዘብ ምንጩ በዋነኛነት ከዓለም ባንክ እንደሆነ የተረዱት አቶ እስክንድር ከዚህ አንጻር ሊያከናውኑ ስላሰቡት ሥራ አስፈላጊውን ነገር ማጥናት ጀመሩ።

ስለዚህ ይህንን አጋጣሚ እንደ ትልቅ እድል በማየት በአዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ምን ያህል ይዞታ ላይ እንደሰፈሩ ጥናት ማድረጋቸውን ይናገራሉ።

እንደ አቶ አስክንድር ጥናት "በአዲስ አበባ አንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት 42000 ስኩዌር ካሬ ሜትር ላይ ሰፍሮ ይገኛል።"

ይህ በክልል ከተሞች እና በገጠሪቷ የአገሪቱ ክፍል በጣም እንደሚለይ ይናገራሉ።

ስለዚህ ይህንን እንደ መነሻ በመውሰድ እና በየትምህርት ቤቱ ከ10 የሚበልጡ ወላጆችን በማደራጀት ወደ ሥራ የጓሮ አትክልት ልማት ሥራውን ማከናወን ጀመሩ።

አግሮኖሚስቱ [የአፈር ጥበቃና የአዝርዕት ባለሙያ] አቶ እስክንድር የትምህርት ቤቶቹን የምገባ ፕሮግራም እንዲያግዝ በማሰብ በ10 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የጀመሩት የተለያዩ የጓሮ አትክልቶች ማልማት ውጤት ማሳየት ጀምሯል።

በአንድ ትምህርት እስከ 12 ኩንታል ድንች ማምረት ችለናል የሚሉት አቶ እስክንድር፣ በተጨማሪም የዶሮ እርባታ የጀመሩ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

"በዚህ መልኩ የተማሪዎች ምገባ ራሱን እንዲችል ማድረግ ይቻላል" የሚሉት አቶ እስክንድር፣ አልፎ ተርፎም ከዚያ ላይ በሚገኘው ገቢ ወላጆች እና ተማሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ይናገራሉ።

አቶ እስክንድር ማን ናቸው?

አቶ እስክንድር በሙያቸው አግሮኖሚስት ናቸው። "ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ ነው የመጀመሪያ ዲግሪዬን ያገኘሁት" ይላሉ።

ኡጋንዳ ውስጥ ለሰባት ዓመታት በአንድ መንግሥታዊ ባልሆነ ደርጅት ውስጥ ተቀጥረው ሰርተዋል። ከዚያም ውጪ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና በደቡብ ሱዳን በግብርናው ዘርፍ ሰፊ ልምድ አካብተዋል።

በኡጋንዳ በነበራቸው ቆይታ ግብርና ተገቢውን ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ፣ የከተማ ግብርና ደግሞ እጅጉን ተስፋፋቶ፣ እንዲሁም የሚገባውን ያህል የከተሜው ሕይወት ላይ ለውጥ አምጥቶ ማስተዋላቸውን ይናገራሉ።

ኡጋንዳ ውስጥ በየጓሮው ባለው የበሬ ግንባር በምታክል ቦታ አትክልቶችን በመትከል ራሱን የሚመግብ ሕዝብ በርካታ መሆኑን ይናገራሉ።

ይህንን ተሞክሮ "በአገራችን ባህል እንዲሆን ፈለግኩ" የሚሉት አቶ እስክንድር፣ ከግብርና ጋር ከፍተኛ የተቆራኘ ሕይወት ያለው ሕዝብ ነገር ግን በምግብ ዋስትና ጥያቄ ላይ መውደቁ ያሳስባቸዋል።

አግሮኖሚስቱ እስክንድር በኡጋንዳ ያዩትን መልካም ተሞክሮ ወደ አገር ቤት በማምጣት በትምህርት ቤቶች ላይ መጀመራቸውን ይናገራሉ።

ለዚህም እንዲረዳቸው በትምህርት ቤቶች የምግብ አቅርቦት ዙሪያ የሚሰራውን 'ፉድ ሴኪዩርድ ስኩልስ አፍሪካ' [Food Secured Schools Africa (FSSA)] የተሰኘ ድርጅት መሰረቱ።

ይህንንም ጽንሰ ሃሳብ ለማስለመድ ዝነኛ ሰዎች በየጓሯቸው አትክልቶችን በመትከል ምሳሌ እንዲሆኑ መሞከራቸውን ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ የሚኖሩ አብዛኛው ነዋሪዎች ሰፊ ሆነ ግቢ ይዘው እንደሚገኙ የሚያስረዱት አቶ እስክንድር፣ በአግባቡ እነዚህን ስፍራዎች ለከተማ ግብርና በመጠቀም በምግብ እህል ራስን መቻል እንደሚቻል ያስረዳሉ።

አክለውም የከተማ ግብርናን የሕይወት ዘዬ በማድረግ፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ እንደሚቻልም ይናገራሉ።

ግብርናን እንደ ቢዝነስ ማሰብ እንደሚያስፈልግ፣ በግብርና ሰርቼ እበለጽጋለሁ የሚል ትውልድ መፈጠር እንዳለበትም ያምናሉ።

"የኢትዮጵያ ግብርና በአግባቡ ከተያዘ የዳቦ ቅርጫት መሆን ትችላለች" የሚሉት አቶ እስክንድር፣ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ጎረቤቶቿን መመገብ እንደምትችል ሲናገሩ በልበ ሙሉነት ነው።

በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የክልል ከተሞች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት፣ የእምነት ቦታዎች፣ ትምህርት ቤቶች ሰፋፊ ቦታዎችን አጥረው መያዛችን በማስታወስ፤ እነዚያን ስፍራዎች ለከተማ ግብርና ማስፋፊያነት በአግባቡ ማዋል ከተቻለ በምግብ እህል ራስን መቻል ቀላል ነው ይላሉ።

ይህንን በማድረግ የአርሶ አደሩን ጫና መቀነስ ከቻልን እርሱ ወደ ሐብት ማፍራት ይሄዳል የሚሉት አቶ እስክንድር ይህም በምግብ ዋስትና ላይ እንዳይቆይ ከተሜው ሊያግዘው እንደሚገባ ይናገራሉ።

"አርሶ አደሩ ደከመኝ ሰልቸኝ ሳይል ሰርቶ ከተሜውን ጨምሮ ይመግባል" የሚሉት አቶ እስክንድር፣ አሁን ግን በአየር ንብረት ለውጥ፣ የተለያዩ ግብዓቶችና ቴክኖሎጂዎች ባለመሟላት ለራሱም እጅ ሲያጥረው ነው በማለት፤ "ስለዚህ ከተሜው አርሶ አደሩን በከተማ ግብርና ሊያግዘው ይገባል" ይላሉ።

"በግብርናም ሚሊየነር መሆን ይቻላል" በማለትም፣ በአስሩ ትምህርት ቤቶች ካሏቸው የከተማ ግብርና ፕሮግራሞች በተጨማሪም በግላቸው ከዚሁ ጋር የተያያዙ ሌሎች ሥራዎች ላይ መሰማራታቸውን ይናገራሉ።

በአሁኑ ጊዜ አንድ የአቡካዶ ችግኝ በ40 ብር በመሸጥ ገቢ ማግኘት ይቻላል የሚሉት አቶ እስክንድር፤ በመጋቢት 28 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ብቻ 5000 የአቦካዶ ችግኞች አፍልተው ለሽያጭ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

በዚህ ሥራ ላይ 15 ወላጆች በአማካይ በትምህርት ቤት ውስጥ እየሰሩ ይገኛሉ።

በግላቸው ደግሞ በ300 ካሬ ሜትር ላይ 10 ሺህ የአቦካዶ ችግኞችን በማፍላት ለገበያ አቅርበዋል።

አቶ እስክንድር ችግኞችን በመሸጥ፣ በጓሮ አትክልት ልማት ላይ ለመንግሥታዊ ድርጅቶች ስልጠናዎችን በመስጠት ገቢ እንደሚያገኙም ይገልጻሉ።

የከተማ አርሶ አደር

አግሮኖሚስቱ አቶ እስክንድር ከኡጋንዳ መጥተው የምሥራቅ አፍሪካ አገራትን መልካም ተሞክሮ በአገራቸው ተግባራዊ ለማድረግ ደፋ ቀና ሲሉ የገጠማቸው የመጀመሪያ ፈተና "ግብርና በከተማ እንዴት ሲደረግ?" የሚለው ነበር።

መጀመሪያ ሥራውን ሲጀምሩ ትግሉ ከባድ እንደነበር የሚያስታውሱት ባለሙያው፣ የመጀመሪያው ተግዳሮት "ግብርና መሬት ይፈልጋል። ከከተማ ወጣ ተብሎ የሚሰራ ሥራ ነው" የሚለው መሆኑን ይናገራሉ።

ግብርናን በትልቅ መሬት ብቻ ማሰብ ከፍተኛ ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር አክለው ተናግረዋል።

ራስን ለመመገብ በትንሽ መሬት ላይ ምርት ማምረት ይቻላል የሚለው አስተሳሰብ በሂደት እያደገ የመጣ መሆኑንም ይገልጻሉ።

የከተማ ግብርና ተገቢው ትኩረት አላገኘም የሚሉት አቶ እስክንድር፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የጀመሯቸው የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴዎች እና ኮሮናቫይረስ ሰውን ወደ ጓሮው እንዲመለከት እንዳደረገው ይጠቅሳሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ግን ያለው የኢንሹራንስና የፋይናንስ ሥርዓት ገበሬውን የሚያበረታተ እንዳልሆነ የራሳቸውን ተሞክሮ በመጥቀስ ያስረዳሉ።

አቶ እስክንድር በግላቸው ወደ 10 ሺህ አቦካዶ አምርተው ባንኮች ያንን በመያዝ ብድር እንዲሰጧቸው እንዲሁም ዶሮ እርባታ እና የዶሮ መኖ ማምረት ለመጀመር ቢጠይቁም 10 ሺህ ችግኝ ማስያዣ አይሆንም መባላቸውን ያስታውሳሉ።

አገራችን ከተማን ማዕከል ያደረገ፣ ለገበሬውን ትኩረት ያላደረገ "የተዘጋ የፋይናንስ ሥርዓት" ያላት ናት በማለትም ይህ የፋይናንስ እና የኢንሹራንስ ሥርዓት መስተካከል እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

አርሶ አደሩን ሰርቶ እንደሚቀየር፣ ሥራ ፈጣሪ መሆኑን በማመን ይህንን ማዘመን እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።